ሙሉ የመዝገብ ስሙ ኤድሰን አራንተስ ዶ ናሲሜንቶ ነው፡፡
ኤድሰን የተባለው ወላጆቹ የኤሌክትሪክ ኃይልን የፈጠረው ቶማስ ኤድሰን አድናቂ በመሆናቸው ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ጓደኞቹ ‹‹ፔሌ›› የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶ በመላ ዓለም የናኘ ስም ሆነ፡፡
ከትምህርት ጎን ለጎን ሻይ እየሸጠ፣ በአንድ ካልሲ እንዲሁም ያለ ምቹ ጫማ እግር ኳስ መጫወት የጀመረው ፔሌ የእግር ኳስ ተመልካቹን ያስደነቀ ተጨዋች ነበር፡፡
አብዛኛውን የተጨዋችነት ዘመኑን በብራዚሉ ሳንቶስ ነው ያሳለፈው፡፡ ስድስት የብራዚል ሊግ ዋንጫን ከሳንቶስ ጋር አንስቷል፡፡
ፔሌ ከሐገሩ ብራዚል ጋርም እ ኤ አ የ1958፣ 1962 እና የ1970ውን የዓለም ዋንጫ አሸንፏል፡፡ በአጠቃላይ አንድ ሺ 363 ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ሺ 279 ግቦችን በማስቆጠር በዓለም ጊኒስ መጽሐፍ ላይ ስሙ ሰፍሯል፡፡ በሁለቱም እግሮቹ መጫወት የሚችል፣ ያገኛቸውን የግብ እድሎች የማያባክን ስኬታማ ተጨዋች ነበር፡፡
ፔሌ ከእግር ኳስ ጨዋታ ከተገለለ በኋላ ከ1995 እስከ 1998 ድረስ የብራዚል ስፖርት ሚኒስትር ሆኖ ሀገሩን አገልግሏል፡፡ በስልጣን ዘመኑ በሀገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ የነበረውን ብልሹ አሰራርና ሙስና የታገለና የቀነሰ ስኬታማ መሪ ነበር፡፡
በ1977 በገጠመው ህመም አንድ ኩላሊቱን በቀዶ ጥገና ያስወጣው ኤድሰን አራንተስ ዶ ናሲሜንቶ ፔሌ በተደጋጋሚ ሆስፒታል ገብቷል፡፡
ፔሌ በ2018ቱ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ዊልቼር ላይ ተቀምጦ ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከርሱ ተቀናቃኝ ማራዶና የተነሳውን ፎቶ ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡
ኤድሰን አራንተስ ዶ ናሲሜንቶ (ፔሌ) ሶስት ጊዜ ትዳር መስርቶ ሰባት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ፔሌ በትልቁ አንጀት ካንሰር ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ በተወለደ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ታህሳስ 29 2022 በብራዚል ሳኦ ፖሎ ነበር፡፡ የተወለደው ደግሞ ከ85 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ነበር።
በታምራት አበራ