በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራን፣ ዘላቂ መሠረተ ልማቶችንና የሰው ሃይል ልማትን ለማስቀጠል የዓለም ባንክ ቀጣይ ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገለፀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ጉዳዮች ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስ አና ብጄርዴ ጋር በቅድመ-ልማት ፕሮጀክቶች፣ በመካሄድ ላይ ያሉ የሪፎርም ስራዎች እና አዳዲስ የፋይናንሲንግ ዘዴዎች ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ከፍተኛ ደረጃ ያለው ውይይት አደርገዋል።
ውይይቱ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2025 ከተካሄደው የአለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ግሩፕ አመታዊ ስበሰባ ጎን ለጎን ነው።
በዚህ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ፤ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ ለማሳደግ ያለውን ከፍተኛ ሚና እውቅና በመስጠት እየተደረገ ለሚገኘው የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ አመስግነዋል።
ባንኩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማዘመን፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ አዳዲስ የእድገት መንገዶችን በመፍጠርና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን በማጎልበት የስራ እድል ለመፍጠር እና የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ያለውን አስተዋፅዖም አንስተዋል።
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ከፍተኛ ድጋፍ እየተካሄዱ በሚገኙ ዋና ዋና ዘርፎች ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍን በማረጋገጥ ላሳየው አጋርነት ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የስራ እድል ፈጠራን፣ ዘላቂ መሠረተ ልማቶችንና የሰው ሃይል ልማትን ለማስቀጠል የባንኩ ቀጣይ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መግለጻቸው መመላከቱንም ኢዜአ ዘግቧል።
የአለም ባንክ የስትራቴጂክ አጋርነት ኦፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሚስ አና ብጄርዴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባካሄደው የሪፎርም አጀንዳ ምክንያት የተገኘውን ውጤት አድንቀዋል።
በሪፎርሙ አማካኝነት የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን፣ ከፍተኛ የወጪ ንግድ መጨመሩን በተለይም በወርቅ፣ የተሻለ የሀገር ውስጥ ገቢ ማሰባሰብን የሚያጠናክር እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ ምቹ የንግድ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ለማሳያነት አንስተዋል።
ዋና ዋና የሪፎርም ርምጃዎችን በመተግበር ረገድ መንግስት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያበረታቱም ገልጸዋል።