የኢትዮጵያ መንግስት የፊስካል አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብን ለማጎልበት እና ቁልፍ መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎች ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
በአቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በኢኮኖሚ ሪፎርም ሂደት እና ከአይ ኤም ኤፍ አመራር ጋር ያለውን ቀጣይ አጋርነት በተመለከተ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና ከአይ ኤም ኤፍ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ቀጣይነት ላለው ድጋፍ አመስግነው፣ መንግስት የፊስካል አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብን ለማጎልበት እና ቁልፍ መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎች ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኝነትን በአጽንኦት አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ያላትን የቆየ አጋርነት ከፍ ያለ ግምት ትሰጣለች ያሉት ሚኒስትሩ በማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ደፋር የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል።
የአይ ኤም ኤፍ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ እነዚህን አላማዎች ለማሳካት አጋዥ ሆነው እንደቀጡም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
እየተካሄደ ባለው የሪፎርም ማዕቀፍ ውስጥ ሰፊ የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎች አካል በመሆን የኢትዮጵያን አወንታዊ የኢኮኖሚ እይታ እና የመንግስት የማህበራዊ ወጪ መጨመርን በተመለከተ ለዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን የለውጥ ጥረቶች ግስጋሴ እና ስኬት በማጉላት ለስኬቶቹ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ቁልፍ ጉዳዮችን አቶ አህመድ ሽዴ ያብራሩ ሲሆን ለስኬቶቹ መነሻ የሆኑ ተግባራትንም አንስተዋል።
በከፍተኛ የመንግስት እርከኖች ጠንካራ ባለቤትነት እና ቁርጠኝነት፣ በሁሉም የመንግስት አካላት ሁሉን አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ እና ትግበራ፣ በጥንቃቄ የተነደፉ ቅደም ተከተል ያላቸው የሪፎርም እርምጃዎችን በሚገባ ማዘጋጀት፣ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ውጤታማ የግንኙነት እና የማህበራዊ ጥበቃ ዘዴዎች እንዲሁም ከልማት አጋሮች በተለይም ከአይ ኤም ኤፍ፣ ከአለም ባንክ እና ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ዋና ዋናዎቹ ተጠቃሽ እርምጃዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዋን የበለጠ ለማራመድ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም እና ዘላቂነት ፋሲሊቲ (Resilience and Sustainability Facility (RSF)) ለማግኘት ያላትን ከፍተኛ ፍላጎትም በአጽንኦት አንስተዋል።
የሁለትዮሽ እና የንግድ አበዳሪዎች ጋር እየተደረገ ስላለው የዕዳ አያያዝ ውይይቶችን በተመለከተ ለአይኤምኤፍ የስራ ሀላፊዎች ወቅታዊ ማብራሪያ የሰጡት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ናቸው።
እስካሁን የተገኘውን አበረታች እድገት በመጥቀስ በዚህ ሂደት ውስጥ የአይ ኤም ኤፍ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊነትን በተመለከተም እንዲሁ አጽንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።
የአለም ገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ክፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በአይ ኤም ኤፍ ለሚደገፈው የሪፎርም ፕሮግራም ጠንካራ ትግበራ ከፍተኛ አድናቆት እና ምስጋና አቅርበዋል።