የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ስልጣኔ እንዲሁም እድገት በመወሰን ቋንቋ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይነገርለታል።
ከግለሰባዊነት ወደ ቤተሰባዊነት ቀጥሎም ወደ ማህበረሰባዊነት እና ሀገርን ወደ መመስረት የሰው ልጅ በነበረው እድገት ብሎም የጋራ ስልጣኔ እና ማንነትን ለመፍጠር ቋንቋን በሰፊው ተጠቅሟል።
በዕለት ከዕለት መስተጋብር ፣ በስራ እና ህይወት የተሳካ ግንኙነትን ለማሳለጥ ቋንቋዎች ከነበራቸው ሚና በዘለለ አሁን የተደረሰበት እጅግ የተራቀቀ አለም ያለተግባቦት የሚታሰብ አይደለም። በባህል ፣ በኢኮኖሚ ፣ በፖለቲካ የበላይነት እና በቅኝ ግዛት ከቦታ ቦታ የተስፋፉት ቋንቋዎች በርካታ ተናጋሪዎችን ማፍራት ችለዋል፡፡
በዚህ የተነሳም በአለም አቀፍ ደረጃ 7 ሺህ ቋንቋዎች ቢኖሩም የምድር ግማሽ የሚሆነው ህዝብ የሚናገራቸው ቋንቋዎች ብዛት 23 ብቻ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንግሊዘኛ ፣ ፖርቺጊዝ ፣ ፍሬንች ፣ ስፓኒሽ እና ሌሎችም ቋንቋዎች አፋቸውን ከፈቱባቸው ዜጎች ባለፈ በአፍሪካ እና በሌሎች የአለም ክፍሎች በርካታ ተናጋሪዎች አሏቸው፡፡
1.42 ቢሊየን ወይም የምድር 19 በመቶ ህዝቦች የሚናገሩት እንግሊዘኛ ቋንቋ በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ተናጋሪዎችን በመያዝ ቀዳሚው ነው፡፡ 390 ሚሊየን በቋንቋው አፋቸውን የፈቱ ተናጋሪዎች ሲኖሩት 1.12 ቢሊየን ሁለተኛ ደረጃ ተናጋሪዎችን አፍርቷል፡፡
በ5ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ እንደተፈጠረ የሚነገርለት ቋንቋ በአሁኑ ወቅት በ67 ሀገራት ይፋዊ የስራ ቋንቋ በመሆን እንደሚያገለግል ስታቲስታ ኢትኖሎጂን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ ያመላክታል። በአለም ላይ በስፋት ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል 1.38 ቢሊየን ተናጋሪዎችን በመያዝ በሁለተኛነት የሚገኝው በቻይና እና በሌሎች የእስያ ሀገራት የሚገኝው ማንዳሪን ቋንቋ ነው፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የሚገኝው ሂንዲ ሲሆን ቋንቋው በህንድ ከሚገኙ 22 ይፋዊ የስራ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው፤ የቋንቋ ሀብታም በሆነችው ህንድ እንግሊዘኛን ጨምሮ 121 ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ ስፓኒሽ ፣ ፍሬንች እና አረቢክ ከአራት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ በቅኝ ግዛት ተስፋፍተዋል የተባሉት ስፓኒሽ እና ፍሬንች ቋንቋዎች እያንዳንዳቸው በ21 እና በ29 ሀገራት ይነገራሉ፡፡
በዳዊት በሪሁን