የአእምሮ ጤና እንዴት ይጠበቃል?

You are currently viewing የአእምሮ ጤና እንዴት ይጠበቃል?
  • Post category:ጤና

AMN- ጥቅምት 13/2018 ዓ/ም

አንድ ግለሰብ አስተሳሰቡን፣ ባህሪውን እና ስሜቱን በጥንቃቄ ሲይዝ ጤናማ አእምሮ ይኖረዋል፡፡

የአእምሮ ጤናን ለመጠበቅ፤ አስተሳሰብን ከሚያውኩ፣ ስሜትን ከሚበርዙና አዎንታዊ የሆነውን ባህሪይ ወደ አሉታዊ እንዳይለውጥ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡

የሰው ልጅ ለአካሉ ንጽሕና እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ ለአስተሳሰቡ፣ ለስሜቱ እና ለባህሪይው ጭምር ንጽሕና እንደሚያስፈልገው የስነ-ልቦና ባለሙያው አቶ ሞገስ ገ/ማሪያም ከኤ.ኤም.ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

እንደ አካላዊ ጤንነት ሁሉ ለአእምሮ ጤንነትም በስፖርት የዳበረ ሰውነት፣ የተመጣጠነ አመጋገብ መጠቀም ለስሜት፣ ለአስተሳሰብና ለባህሪይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት ፡፡

በቂ እንቅልፍ መተኛት ሁሉም እንደየእምነቱ ፀሎት ማድረግ እና ሌሎች ማህበራዊ በጐ ልምዶችን መፈፀም የአእምሮ ንጽህናን በመጠበቅ ጤናማ እንደሚያደርጉ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ቤተሰብ ውስጥ ያለውን መስተጋብር ጤናማ ማድረግና እርስ በእርስ ያለውን ግንኙነትን ማጠናከር፣ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሁኔታ መኖር ለአእምሮ ንጽሕና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

ምንም እንኳን እንደግለሰብ የልቦና ውቅር ቢኖርም እንደ ማህበረሰብና እንደ ሀገር የጋራ እሴቶች እና የልቦና ውቅር ላይ ትኩረት አድርጐ መስራት ያስፈልጋል፡፡

በሌሎች የዓለም ሀገራት የማህበራዊ እና የአእምሮ ደህንነት ትምህርት ይሰጣል ያሉት ባለሙያው፤ በእኛ ሀገርም ይህንን ልምድ ቀምሮ መጠቀም ለአእምሮ ጤንነት ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የግብረገብ ትምህርት ተብሎ ይሰጥ እንደነበር የስነ- ልቦና ባለሙያው አንስተው፤ ይህም ከአእምሮ ጤንነት ጋር በእጅጉ ቁርኝት እንደነበረው ገልፀዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ያለ ምንም ማጣራት በማየትና በመስማት ሁሉም ወደ አእምሮ ስለሚገቡ ለአእምሮ ጤንነትና ንጽህና ትልቅ ችግር ይፈጥራሉ፡፡ በመሆኑም የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሊ ባለሞያው ገልፀዋል ፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review