ሰፈራቸው የጠፋባቸው ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ

You are currently viewing ሰፈራቸው የጠፋባቸው ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ

AMN – ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም

ሰው እንዴት የተወለደበት እና ያደገበት ሰፈር ይጠፋዋል ትሉ ይሆናል፡፡ ከረጅም ዓመታት የውጭ ሃገር ቆይታ በኋላ ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ዳያስፖራዎች ግን እዉነትም ሰፈራቸዉ እንደጠፋባቸዉ ከ ኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናረዋል፡፡

በዳያስፖራ ህይወት ቆይታቸው በሰው ሃገር የሚያዩትን መልካም ነገሮች ሁሉ በሃገራቸው ለማየት የሁል ጊዜ ምኞታቸው እንደነበረ ይገልጻሉ፡፡

ታዲያ ለዘመናት እንቅልፍ ተጫጭኗት የነበረችው አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ስራዎች ተሰርተው፣ ተለውጣ ምኞታቸው እውን ሆኖ በማየታቸው የፈጠረባቸው ስሜት ከቃላት በላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቀደመ ሰፈራቸውን ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያስታውሱት ዳያስፖራዎቹ ፤ “ከዓመታት በፊት ያደናቀፈህን ድንጋይ እንኳን ከብዙ ቆይታ በኋላ ስትመለስ ልታገኘዉ ትችላለህ ይላሉ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ለውጥ የሚለው ቃል ከቃል በላይ አልፎ ሰፈራችን ተቀይሮ ሌላ ዓለም ሆኗል” ብለዋል፡፡

በካዛንቺስ የተገናኙት ዳያስፖራዎቹ ተሰባስበው ፒያሳና አራት ኪሎንም ጎብኝተዋል፤ ታዲያ ከጎብኝዎቹ አንዱ የሆነው ቢኒያም ጌታቸው ኑሮውን በካናዳ ቶሮንቶ ካደረገ 30 ዓመት ሆኖታል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር አካባቢ በተደጋጋሚ እመጣ ነበር ያለዉ ዳያስፖራዉ ፤ የበፊቷና የአሁኗ አራት ኪሎ የሁለት ዓለም ሰፈሮች ናቸው፤ እጅግ አምራና ተውባ ነው ያገኘኋት” ሲል ተናግሯል፡፡

ገና በ14 ዓመቱ በታዳጊነት ዕድሜው ከአዲስ አበባ የወጣው ሌላኛው ዳያስፖራ ዮሃንስ አምደብርሃን አሁን ላይ ነዋሪነቱ በካናዳ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ በተለያየ ጊዜ ይመጣ እንደነበር ይናገራል፡፡

ፒያሳ ተወልዶ ያደገው ዮሃንስ፤ የቆሻሻ መጣያ፣ ገደላገደል እና የጅቦች መናኸሪያ የነበረችው ፒያሳ አሁን ላይ ዘመናዊ የእግረኞች የሳይክል መንገድ፣ ሰፋፊ ጎዳናና የልጆች መዝናኛ መጫዎቻ እንዲሁም ቀልብን የሚገዙ ማረፊያዎች ተሰርተውባት በማየቴ ተደስቻለሁ ብሏል፡፡

ከሃገረ እንግሊዝ የመጡት ወይዘሮ አይሻ ረዲ በበኩላቸዉ አሁን ላይ ከኛ አልፎ ለልጆቻችን የሚተርፍ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ቦታዎች መገንባታቸዉ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል፤ በሌላው ዓለም የምናየውና በሃገራችን ሆኖ ለማየት የምንሻው የልማት ስራ ተሰርቶ በማየታችን ኮርተናል ብለዋል፡፡

ጎብኝዎቹ እንደተናገሩት ከሆነ “ከዓመታት በፊት ከሃገር የወጣን ዜጋ አሁን ፒያሳ ላይ አምጥተህ የት ነው ያለኸው ብትለው በእርግጠኝነት ሰፈሩ ይጠፋበታል” ፡፡

እኛም በተሰራው ስራ ሰፈሮቻችንን ለመለየት ተቸግረን ነበር፤ ነገር ግን አሁን ላይ ሰፈራችንን ፈልገን አግኝተናል፤ በአዲስ አበባ በተሰሩ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች የከተማዋ ገፅታ እና ውበት ዘመኑን የሚመጥን ሆኖም አግኝተነዋል፤ በዚህም ኮርተናል ፤ ይህንን የሰሩ እጆች ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review