የቀና ልቦቹ አበርክቶ

You are currently viewing የቀና ልቦቹ አበርክቶ

“በበጎነት ስራዎች የብዙዎች እንባ ታብሷል፤ ይህ አርአያነት ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል”

                                                                 የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

የሀገሬ ሰው “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” ይላል፡፡ እውነት ነው፤ ፈረሱ ቢሻው ያርጅ፣ ቢለውም ይሰበር ዋናው ነገር አብሮነትን፣ መተሳሰብን እና ፍቅርን መሰረት አድርጎ ከልብ የመነጨ የወዳጅ ስጦታ በመሆኑ ዋጋው ከፈረሱ በላይ ነው፡፡

መልካምነት፣ መረዳዳትና ስጦታ ምን ያህል አብሮነትን ማጎልበቻ፣ መለያየትን መርቻ፣ ፍቅርን ማሰንበቻ ድንቅ መሳሪያዎች እንደሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ ይናገራሉ። በተለይ ይላሉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ቸግሯቸው፣ አይዟችሁ ባይ አጥተው የመከራ ቀንበርን ብቻቸውን የሚገፉ ሰዎችን አለንላችሁ ብሎ የሚለብሱት የሚቀምሱት እንዳያጡ ማድረግን የመሰለ ትልቅ ነገር የለም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግስት ደረጃ ሳይቀር ማዕድ ማጋራት፣ በዓላትን አብሮ ማሳለፍና ማህበራዊ ፍትሕን የሚያረጋግጡ ስራዎችን የማከናወን ልምድ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህ ተግባር በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ጎልቶ ይታያል፤ ከ35 ሺህ በላይ የዕለት ጉርስ ያጡ ሰዎች በልተው የሚያድሩባቸው የምገባ ማዕከላት ተከፍተው የብዙዎችን ችግር እያቃለሉ ነው፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ባዶ የምሳ ዕቃ ይዘው ይሄዱበት የነበረው አስከፊ ታሪክ ተለውጦ በትምህርት ቤቶቻቸው እየተመገቡ ነው፡፡ ይህም የቀደመ መረዳዳታችን፣ መተሳሰባችን እና አንዳችን ለአንዳችን መቆማችንን የሚመሰክር መሆኑን ጠቅሰው፣ ተግባሩ መረዳዳትን፣ አብሮ መቆምን ችግርን በጋራ ተካፍሎ ማለፍን የተረዳ ትውልድን ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጥናት መምህርና ተመራማሪ ጉተማ ኢማና (ዶ/ር) በጎነት፣ እርስ በእርስ መደጋገፍና መጠያየቅ ወዳጅነትን ያጠነክራል፤ አብሮነትን ያጎለብታል፤ በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ መከባበርና መደጋገፍ እንዲኖር የሚያደርግና ይበልጥም የአንድን ማህበረሰብ የጋራ እሴት (Social capital) የማጠናከር እና የማሳደግ አቅም እንዳለውም ገልፀዋል፡፡

መረዳዳት፣ መደጋገፍ፣ ማዕድ ማጋራት እና ስጦታዎችን መሰጣጠት እንዲሁም የችግረኞችን እንባ ማበስ የማህበረሰቡን መስተጋብር የሚያበለፅጉ እና አብሮ ለመኖርም ትልቅ ምሶሶ የሚሆኑ ናቸው። በተለይም ይላሉ ጉተማ (ዶ/ር) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ማዕድ የማጋራት፣ ችግረኞችን የመጠየቅና መደገፍ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይታያል፡፡

በተለይም በበጎ ፈቃድ የተሰማሩ ልበ ቀናዎችንም እውቅና የመስጠትና የማበረታታት ስራዎች መከናወናቸው የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህም የማህበረሰቡን ትስስርና መስተጋብር የበለጠ የሚያጎለብት እንደ ሀገርም ትልቅ አቅምን የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዕውቁ የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪው አሚታይ ኢፂዮኒ እ.ኤ.አ በ1993 የማህበረሰብ መንፈስ (The Spirit of Community) የተሰኘ ድንቅ መፅሐፍ አሳትመዋል፡፡ በዚህ ጥናታዊ መፅሐፍ እንደሰፈረው ጠንካራ ሀገር የሚገነባው ዜጎች እርስ በርሳቸው መተሳሰብ፣ መደጋገፍ እና የሞራል ቁርጠኝነት ሲኖራቸው ነው። በመሆኑም ሌሎችን መርዳት ከመደብና ከብሔር ወሰን የዘለለ የጋራ ማንነትን ያዳብራል። ይህም ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ያግዛል ብለዋል፡፡

የሰው ልጅ ሲተባበር ከጭድ ውስጥ መርፌ፣ ከችግር ውስጥ መፍትሔን ያወጣል፡፡ ይህንን በውል የተገነዘቡ ሀገራትና ከተሞች ህዝባቸውን በማሳተፍ ማህበረሰባቸውም የአንድነትን ጉልበት በወጉ በመረዳት በምድራችን ገናና ታሪክን ማስመዝገብ እንደቻሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ መጋቢት 2025 የከተሞች አስተዳደርና ዕድገትን አስመልክቶ ይፋ ያደረገው ጥናታዊ ሪፖርት ያመላክታል፡፡

“ከፍተኛ የማህበረሰብ ተሳትፎ ያላቸው የዓለም ከተሞች፤ ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማትን ማሳደግ ችለዋል” የሚለው መረጃው ለኑሮ ምቹና ተስማሚ፣ ችግርን የሚቋቋሙ እና ዘላቂ ከተሞችን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰብ ተሳትፎ መሰረታዊ የከተማ አስተዳደር ምሰሶ እንደሆነም መረጃው ያመላክታል፡፡

በዓለም ዙሪያ ያሉ ከተሞች ዜጎችን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ማሳተፍ፣ በመንግስት እና በማህበረሰቦች መካከል ትብብርን መፍጠር እና ሁሉን አቀፍ የልማት ውጥኖችን ማስተዋወቅ እና በበጎ ፈቃድ ስራዎች የሚሳተፉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እውቅና እና ሽልማት መስጠት ያለውን ሀገራዊ ጠቀሜታ እየተገነዘቡ እንደሆነ የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ጥናታዊ ሪፖርት በተምሳሌትነትም የቪዬና፣ ሜደልሊን እና ፖርትላንድ ከተሞችን ጠቅሷል፡፡

በአዲስ አበባም የበጎ ፈቃድ ስራ በተደራጀ መልኩ እየተመራ መሆኑን እና እንደ ከተማ አስተዳደሩም በበጎነት የተሰማሩ ልበ ቀናዎችን በመደገፍና በማበረታታት የበርካቶችን እንባ ማበስ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ 11 ቀን 2018 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ለተሰማሩ በጎ ፈቃደኞች “መስጠት አያጎልም’’ በሚል መሪ ሀሳብ የእውቅና መርኃ ግብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ማካሄዱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ ከሰባት ዓመታት ወዲህ በወጣቶቿ፣ በባለሃብቶቿ፣ በመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና በአጠቃላይ በነዋሪዎቿ ከበጋ እስከ ክረምት እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ የዘለቀ የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ መገለጫ ተምሳሌት እየሆነች ትገኛለች ብለዋል፡፡

አክለውም፣ አዲስ አበባ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ወጣቶቿን፣ ባለሀብቶቿን፣ መላው ነዋሪዎቿን፣ የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ባለቤቶችን በማስተባበር ዓመቱን ሙሉ በዘለቀ የበጎ ፈቃድ ተግባር ውስጥ በማሳተፍ ከ42 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በበጎ ፈቃድ ተግባር በማሰባሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ተችሏል። በ2017 ዓ.ም እንዲሁ ከ16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ለተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንዲውል ተደርጓል። ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር አስተዋፅኦ በማድረግ የዘንድሮውንም ልዩ ሽልማት የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ጉሩፕ ወስዷል ብለዋል።

በነዚህ የበጎ ፈቃድ ስራዎች የበርካታ ዜጎችን እንባ ማበስ መቻሉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ በሰው ተኮርና በበጎ ፈቃድ ተግባራት የተሰማሩ አካላትንና ወጣቶችን ልበ ቀናዎች ናችሁ በማለትም አመስግነዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ባህር ተሻግረውና ሀገር አቋርጠው በበጎ አድራጐት ስራዎች ላይ የሚተጉት ነጮች ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ ሲተረክ እንደነበር ያወሱት ከንቲባ አዳነች፣ ይህንን ትርክት በጎ ፈቃደኞችንና ወጣቶችን በማሰለፍ አፍርሰነዋል፤ የሰብዓዊነት መልካችንንም ገልጠንበታል ሲሉ መስክረዋል፡፡

በመንግስት በጀት ብቻ ሀገር ልትለማ አትችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ የከተማዋ የበጀት ጉድለት በበጎ ፈቃደኞች ቀናነትና በጐ ተግባር ተሟልቶ ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አስችሎናል፡፡ የህይወት ትርጉም አንዱ ከጐደለው ላይ መስጠት ነው፤ ከራስ በላይ ለሌሎች ማካፈል፣ ህመማቸውንና ማጣታቸውን መጋራት የላቀ ስብዕናን ይጠይቃልም ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ልክ እንደናንተ ልበ ቀና መሆን ይፈልጋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባ ከለውጡ ወዲህ ባለሀብቶችን፣ ወጣቶችን እንዲሁም መንግስትና ህብረተሰቡን በማስተባበር ከበጋ እስከ ክረምት የበጎ ፈቃድ መገለጫ ሆናለች ሲሉ አክለዋል፡፡

በዚህም የሀገር ባለውለታዎችና በአስከፊ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች የዘመሙ ጎጆዎች መቃናታቸውን አስታውሰው፣ በበጎነት ስራዎቹም የብዙዎች እንባም መታበሱን እና  ይህ አርአያነት ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተደረገውን የበጎ ፍቃደኞች የእውቅናና የሽልማት መርኃ ግብርን መነሻ በማድረግ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የስነ ልቦና ባለሙያና አማካሪ አቶ ማህደር ሳልህ በበኩላቸው፣ በጎነት ከራስ ቆርሶ ሌሎች የሚደረግ የልብ ስጦታ ቢሆንም ሰጭውንም በስነ ልቦና የጠነከረ ከማድረግ አንፃር እንደ መድኃኒት የሚያገለግል ነው፡፡ በጎ ልቦች ሲበዙ በጎ ማህበረሰብ ይፈጠራል፡፡ በጎ ማህበረሰብ እየሰፋ ሲሄድ እንደ ሀገር ፍቅር፣ አብሮነትና መተሳሰብ እየጎለበተ ይመጣል ብለዋል፡፡

አንድ ሰው የበጎ አድራጎት ተጠቃሚ ሲሆን የሀገር ፍቅሩ ይጨምራል፤ በሀገር ግንባታና አንድነት መጠናከር ላይ ይተባበራል። አንድን ቤተሰብ ማገዝ ሀገርን ማገዝ ነው  ያሉት የስነ ልቦና ባለሙያው ሰዎች በችግራቸው ወቅት በጎ የዋለላቸውን አይረሱም፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ሀገር ከመንግስት ታላላቅ ኃላፊዎች ጀምሮ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ሰዎችን የመርዳት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ይህ ደግሞ ድጋፍ በተደረገላቸው ዘንድ ‘ለካ ለእኔ የሚያስብ ወገን አለኝ’ የሚል እሳቤን ይፈጥራል፡፡ ይህም በሚችሉት ሁሉ ለሀገራቸውና ለወገናቸው በፅናት እንዲቆሙ ያደርጋል፡፡ ሌላውም ቢሆን ‘ነገ እኔ አንድ ነገር ብሆን እንዲህ የሚያግዘኝ ህዝብና መንግስት አለ’ ስለሚል በተሰማራበት ሁሉ የነቃና የበቃ ሆኖ እንዲተጋ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገርን በሁለንተናዊ መልኩ ከፍ ለማድረግ ያግዛል፤ በጎነትም የሀገር ፍቅር መሰረት ነው ብለዋል የስነ ልቦና ባለሙያው፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review