- ቁጠባቸውን ላላቋረጡ ተመዝጋቢዎች እንደሚተላለፉ ተገልጿል
• ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች በመተግበር ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ ጥቅምት 20 ቀን 2023 በኒው ዮርክ ከተማ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ “UN expert urges action to end global affordable housing crisis” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ጥናት በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ጥናታዊ ፅሑፍ መሰረትም በዓለማችን ቤት መስራት አሊያም መግዛት የማይችሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመኖሪያ ቤት ወጪያቸውን መክፈል ባለመቻላቸው ብቻ ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ፣ ይህም ለቤት እጦት መባባስ አስተዋጽኦ ስለማድረጉ በፅሑፉ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ህዝብ በቂ የመኖሪያ ቤት እና መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሌለው የሚያትተው ፅሑፉ፣ ይህም በ2030 ወደ 3 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ይላል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው የባለሙያዎች ጥናታዊ ፅሑፍ “አስተዳደሮች፣ መንግሥታዊ ድርጅቶች እና ተቋማት የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመፍታት የበለጠ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለባቸው”
በዓለማችን የተለያዩ አካባቢዎች አሳሳቢ የሆነው የቤት ችግር በአዲስ አበባ ከተማም የሚታይ ስለመሆኑ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ እና ፍላጎት ለመመለስ የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በመዘርጋት የተለያየ የገቢ መጠን ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የመክፈል አቅም ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት በመገንባት ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት በመንግስት አስተባባሪነት በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች በ14 ዙሮች ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፤ ከ5 ሺህ ቤቶች በላይ በተገጣጣሚ ቴክኖሎጂ እየተገነቡ ይገኛሉ፤ የቤት አቅርቦቱን ለማስፋት በተደረገ ጥረት 60 ሺህ ቤቶች በግሉ ባለሀብት እንዲለሙ ተደርጓል፤ በመንግስት እና በግል ዘርፍ አጋርነት ከ120 ሺህ በላይ የቤቶች ግንባታ ስራ ተጀምሯል፤ በበጎ ፈቃድ ባለሀብቶችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ በመንግስትም ጥረት ከ35 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብቶ በዝቅተኛ ኑሮ ላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡
በ20/80 እና በ40/60 የጋራ ቤቶች ልማት መርኃ ግብሮች ተመዝግበው ሲጠባበቁ ከነበሩ አቅም ያላቸውን 4 ሺህ 318 ነዋሪዎች በ54 ማህበራት በማደራጀት ወደ ግንባታ እንዲገቡም ተደርጓል፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኪራይ የሚቀርቡ ቤቶችንም ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ተመዝግበው የቤት ባለቤት ለመሆን የሚጠባበቁ ነዋሪዎችን በአጭር ጊዜ የቤት ባለቤት ለማድረግ የቤት ልማት አማራጮች በማስፋትና በመተግበር ከምን ጊዜውም በላይ እየተጋ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አስመልክቶ በህብረተሰቡ ዘንድ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ምን ያህል ቤቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ? የጋራ ቤቶቹ ግንባታ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? እስከ ዛሬ ቁጠባቸውን ላላቋረጡ ቆጣቢዎች ቤቶቹ ይተላለፋሉ ወይ? የሚሉትና መሰል ጥያቄዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ለመሆኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን ምላሽ አላችሁ? ሲል የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን ጠይቋል፡፡
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊ ኢንጅኒየር ፈቃዱ አለሙ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ በ20/80 እና በ40/60 መርኃ ግብር ተጀምሮ ተቋርጠው የነበሩትን በማጠናቀቅ ላይ ነን ብለዋል። በመንግስት ካፒታል የተገነቡ 1 ሺህ 287 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በ2017 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡ በዚህ በግማሽ ዓመት እስከ ሰኔ የሚጠናቀቁ በድምሩ ከ3 ሺህ 500 በላይ ቤቶች በግንባታ ላይ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹም በጥቂት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቁና የሚተላለፉ ናቸው ብለዋል፡፡
ቁጠባቸውን ሳያቋርጡ በቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ዘንድ “ቤቱን ይሰጡናል ወይስ አይሰጡንም ይሆን” የሚል ጥርጣሬዎች አልፎ አልፎ ይስተዋላል፤ ለዚህ ምን ምላሽ አለ? ብለን የጠየቅናቸው ኢንጅኒየር ፈቃዱ፣ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ቤቶች ቅድሚያ ለቆጠቡት የሚሰጡ በመሆናቸው ቆጣቢዎች ያለምንም መጠራጠር ቁጠባቸውን ሳያቋርጡ መቀጠል እንዳለባቸው መክረው፣ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቅድሚያ ለቆጠቡ ዜጎች የሚተላለፉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
እንደ ኢንጅኒየር ፈቃዱ ማብራሪያ ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ይፋ እንዳደረጉት በዚህ ዓመት በመንግስት ከተያዙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ የቤት ልማት ነው፡፡ በመጪዎቹ 5 ዓመታት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ይገነባሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ትልቁን ድርሻ ወስዷል። ዘንድሮ ብቻ ለቤቶች ግንባታ በርካታ ቢሊዮን ብር መበጀቱም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ሩብ ዓመትም 6 ሺ 600 ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ በመንግስት ካፒታል ከ20 ሺህ በላይ ቤት ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል፡፡
ባሳለፍነው ረቡዕም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሬትና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮን እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን በ2018 1ኛ ሩብ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት አፈፃፀማቸውን ተመልክተዋል። የመሬትና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶሚ አበበ (ዶ/ር) ቢሮው እና ኮርፖሬሽኑ የመምህራንን የቤት ልማት ጨምሮ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ የጀመሯቸው ተግባራት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎትን በማዘመን፣ ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር፣ ፕሮጀክቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በመምራት እና አማራጭ የቤት ፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ ረገድም የተሻለ አፈጻጻም መታየቱን ገልፀዋል፡፡
በወቅቱም የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛውን ሩብ ዓመት አፈጻጸም ያቀረቡት የቢሮው ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ ቢሮው እና ኮርፖሬሽኑ በዝግጅት ምዕራፍ የቤት ልማት አማራጮችን በማስፋት የቤት አቅርቦቱን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባራትን ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም በመንግስት አስተባባሪነት፤ በመንግስትና በግል አጋርነት በርካታ ቤቶች እየተገነቡ መሆናቸውን እንዲሁም በማህበር የተደራጁ ማህበራትም ግንባታን መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም በበጀት ዓመቱ መንግስት ትኩረት የሰጠውን የቤት ልማት እቅድ ለማሳካት ተቋማቱ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊ ኢንጅኒየር ፈቃዱ አለሙ በዚህ ዓመት በጥቅሉ ከ50 ሺህ በላይ ቤቶችን በመንግስት ካፒታል እናስጀምራለን የሚል ዕቅድ አለ ብለው፣ ከዚህ ጎን ለጎንም በመንግስትና በግል አጋርነት ከባለሀብት ጋርም በጋራ ለማልማት ከ120 ሺህ በላይ ቤቶች ውል ተፈፅሟል፡፡ ከዚህ ውስጥም 10 የሚሆኑ ሳይቶች ላይ ግንባታ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህ ሁሉ ቤት እየተሰራ ያለው ቅድሚያ ቆጣቢውን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ቆጣቢዎች አሁንም ቁጠባቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ ቤቶቹ ሲጠናቀቁ በቁጠባቸው መሰረት ይፋ እየተደረገ እጣ የሚወጣ ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡
በተለይ የኮሪደር ልማት ተነሽዎችን በተመለከተ በ2017 ዓ.ም ብቻ 5 ሺህ 176 ቤቶች ተሰርተው ለተነሺዎች የተላለፈ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም ቆጣቢዎች እንዳሉበትም ጠቁመዋል። በመሆኑም ቤቶቹ እየተላለፉ ያሉት ከተማዋ ላይ ላለ ነዋሪ ሲሆን እየተላለፉ ያሉትም መመሪያን በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ በመሆኑም አሁንም ቆጣቢዎች ቁጠባቸውን እየቆጠቡ ይጠብቁ፣ ልክ ቤቶቹ ሲጠናቀቁ እየተወሰነ የሚተላለፉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በጥቅሉ በዚህ ዓመት የመንግስት አቅጣጫ ልክ በ2016 እና በ2017 ዓ.ም ኮሪደር ልማት ላይ እንደነበረው ትኩረት ቤት ልማት ላይ ያተኮረ ነው፤ ይህንንም ታሳቢ ያደረጉ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ የነበረው ከባንክ በሚገኝ የቦንድ በጀት እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ ደግሞ ከለውጡ በፊት የነበረውን እዳ ሁሉ ይዞ የመጣው ማነቆ እና የስራ ክፍተት የፈጠረ ነበር፡፡ አሁን ይህንን ሁሉ ችግር በመፍታት ነው ወደስራ የተገባው የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት በመንግስት ለቤት ግንባታ ብሎ በጀት እንደማይዝ አስታውሰው፣ አሁን ላይ ግን ለቤት ግንባታ ተብሎ ለብቻው በመለየት ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይያዛል፤ የተጨማሪ በጀት የዕቅድ ማሻሻያ መደረጉንና የከተማ አስተዳደሩም ይህንን ታሳቢ አድርጎ የበጀት ማስተካከያ ማድረጉ የማይቀር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይ ቆጣቢዎች አንዳንዶች በተሳሳተ መልኩ የሚያሰራጩትን የማይሆን መረጃ ባለመስማት እየተገነቡ ያሉ ቤቶች ቆጣቢውን ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ቁጥባቸውን አጠናክሮ በመቀጠል ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚያከናውነው ቤቶች ግንባታ በተጨማሪ የተለያዩ ባለሀብቶችን እና በጎ ፈቃደኛ ዜጎችን በማስተባበር አዳዲስ ቤቶችን በመገንባትና ሊወድቁ የደረሱ ደሳሳ ጎጆዎችን በአዲስ መልክ ቀና በማድረግ የበርካቶችን እንባ እያበሰ መሆኑም ይታወቃል፡፡
በመለሰ ተሰጋ