የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሬ (ፕ/ር)
“የባህር ጠረፍ (ወደብ) ያለህ ሀገር ከሆንክ ዓለምን ታገለግላለህ፤ የባህር በር ከሌለህ ግን ጎረቤትን ስታገለግል ትኖራለህ፡፡” ይላሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ተመራማሪ የሆኑት እንግሊዛዊው ፖል ኮሊየር፡፡ ኮሊየር “The bottom Billion” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዳብራሩት፣ አዳጊና ድሃ ሀገራት ወደፊት እንዳይሄዱ አንቀው ከያዟቸው የልማት ጋሬጣዎች መካከል የባህር በር አለመኖር አንዱ ነው፡፡ የባህር በር ያላቸው ሀገራት በተሻለ ከዓለም ጋር የመገናኘት፣ የመነገድና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ እድል እንዳላቸው ያብራራሉ፡፡
በዓለም ላይ 44 ሀገራት ወደ ባህር መውጫ በር የላቸውም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 32ቱ የተለየ ከበድ ያሉ ፈተናዎች ያሉባቸውና አዳጊ ሀገራት ናቸው። የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ባለፈው ሐምሌ ወር በገፀ ድሩ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከሚገኙ 32 የባህር በር የሌላቸው አዳጊ ሀገራት መካከል 16ቱ በአፍሪካ፣ 10 በእስያ፣ አራቱ በአውሮፓ እና ሁለቱ በላቲን አሜሪካ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ሀገራቱ ከ500 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይኖራል፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን ብናይ በጥንት በአክሱም ዘመነ መንግስትና ከዚያ በኋላ የነበሩ ስልጣኔዎች መሰረታቸው ከባህር ጋር የተቆራኘ ነው። ባህር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭ፣ የህልውና መጠበቂያ አቅም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ሚዛን ማስጠበቂያ እንዲሁም ከውጭ ዓለም ጋር ለሚደረጉ የንግድ ልውውጥ ማሳለጪያ በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እየራቀች በመጣች ቁጥር የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና ራስን የመጠበቅ አቅሟ እየተዳከመ እንደመጣ የታሪክ ባለሙያዎች ያሳያሉ፡፡

ባህር ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ አካል እንደሆነ በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ እና በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የታሪክ መምህርና ተመራማሪ በመሆን የሰሩት አየለ በከሬ (ፕ/ር) ይገልፃሉ፡፡ በዓለም ላይ ዋነኛው የንግድ ልውውጥ መስመር ባህር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የባህር በር በነበራት ጊዜ በስልጣኔና እድገት ወደፊት ሄዳ ነበር፡፡ ከውጭ የሚያስፈልጋትን ዕቃዎች የምታስገባውና የምታስወጣባቸው አማራጭ ወደቦች ነበሯት፡፡ አዶሊስ፣ ዘይላ፣ በርበራ፣ ምፅዋና አሰብ ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ በኋላ ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያ የባህር በሯን አጣች፡፡ ኤርትራ ነፃ በምትወጣበት ጊዜ አሰብ ለኢትዮጵያ ነፃ ወደብ እንዲያገለግል ስምምነት ነበር። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ ይኼ ሁኔታ መቋረጡን “የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” በሚል ርዕስ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ የጥናት ሰነድ ያሳያል፡፡
የባህር በር አለመኖር ምን አሳጣን?
የሀገራት እድገትና ህልውና ከባህር በር መኖርና አለመኖር እንዲሁም ተጠቃሚነት ጋር ይያያዛል፡፡ አብዛኞቹ ያላደጉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የዓለም አቀፍ ገበያን ለመድረስ መዋቅራዊ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዚህ ገፈት ቀማሽ እንደሆነች “የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” ሰነድ ላይ የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ ሀገር ከሆነች በኋላ ለገቢና ወጪ ንግድ አገልግሎት የምትጠቀመው የጎረቤት ሀገራትን ወደቦች፤ በዋናነት የጂቡቲን ወደብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በዓመት ለወደብ ኪራይ ክፍያ እስከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታወጣለች፡፡
የባህር በር አለመኖር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ስጋት መደቀኑን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ማሩ አብዲ ይናገራሉ፡፡ ከሰላሳ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ 1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ ዳርቻ ነበራት፡፡ ከ1983 ዓ.ም በኋላ የባህር በር አልባ ሆነች፡፡ ከቀይ ባሕር 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ጫፍ ላይ የምትገኝ ሀገር ብትሆንም፤ ከሩቅ ያሉ ሀገራት በቀጣናው ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲንቀሳቀሱ ከውጭ የምትመለከት፤ ለኢኮኖሚያዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ስጋት ተጋላጭ የሆነች ሀገር ሆናለች፡፡
“ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ” የተሰኘው የሀሳብ አመንጪ ተቋም በ2014 ዓ.ም ባሳተመው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ “የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ ከጎረቤትና አረብ-ባህረ ሰላጤ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት” በሚል ርዕስ መጣጥፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አስናቀ ከፋለ (ዶ/ር) የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ስትራቴጂካዊ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑና ወደብ አልባ መሆኗ ኢትዮጵያ ላይ ስጋት የሚደቅን መሆኑን አትተዋል፡፡
“የሀገሪቱ መልክዓ-ምድር አቀማመጥ በውጭ ግንኙነቷ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። በመጀመሪያ፣ ኢትዮጵያ የምትገኘው እጅግ ባልተረጋጋውና አውሮፓና እስያን እንደ ድልድይ በማገናኘት ከፍ ያለ ጂኦ-ስትራቴጂክ ዋጋ ባለው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ነው” ይላሉ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ እንዳብራሩት፣ “በቀጣናው ባለው አለመረጋጋት፣ የሽብርና የባህር ላይ ውንብድና ስጋት ምክንያት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሀገራት በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው የጦር ሰፈሮቻቸውን በመመስረት ላይ ናቸው። ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኙበት ሲሆን፣ ወትሮም የመረጋጋት ችግር ባለበት የአፍሪካ ቀንድ የነዚህ የጦር ሰፈሮች መበራከት ለቀጣናው ሰላም ተጨማሪ የስጋት ምንጭ ሆኗል”፡፡

የባህር በር የማግኘት ጥያቄ
ኢትዮጵያ የባህር በር ካጣች በኋላ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የባህር በር ጥያቄን ማንሳት በመንግስት ደረጃ የተዘጋ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ጥያቄውን የሚያነሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሀገር ተቆርቋሪ ዜጎችም ቢሆን በተስፋፊነት ሲፈረጁ ነበር፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሁለት ዓመት በፊት የባህር በር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማንሳታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በመንግስት፣ በማህበረሰቡና በተለያዩ አካላት ትኩረት ስቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በፃፉት “የመደመር መንግስት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የወደብ አለመኖር የኢትዮጵያን እድገት በሁለንተናዊ መልኩ እየገደበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ወደብ ለኢትዮጵያ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ነው። በአፍሪካ ቀንድ ትልቁን ኢኮኖሚን እየገነባን ነው፡፡ በአፍሪካ ከሚገኙ ታላላቅ ኢኮኖሚዎች አንዱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነው፡፡ በአፍሪካ ሁለተኛው የህዝብ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡” ሲሉ ኢትዮጵያ በሚያድገው ኢኮኖሚዋ ልክ የምትጠቀምበት የራሷ የሆነ የወደብ መሰረተ ልማት እንዲኖራት መንግስት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችው አውሮፓውያን በአፍሪካ ቀንድ ያደረጉት የቅኝ ግዛት ውጤትና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትለይ ወደብ እንደሚገባን ጉዳዩን በመያዝ ባለመሰራቱ ነው፡፡” የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሬ (ፕ/ር)፣ ያለባህር በር በእድገትና ስልጣኔ ጎዳና ወደፊት መገስገስ አይቻልም፡፡ የባህር በር ለማግኘት ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ ህጋዊና ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ መቀጠል እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡
የባህር በር አለመኖር በኢትዮጵያ ደህንነት ላይ ስጋት መደቀኑን የሚያነሱት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ማሩ አብዲ፣ የባህር በር ጥያቄው ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ ለማደግና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚቀርብ ነው፡፡ ለዚህም በጉዳዩ ላይ መወያየትና መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡
ከህዝቡ ምን ይጠበቃል?
“ከዚህ ቀደም የነበረው መንግስት በሰራው ስህተት የባህር በር አጥተናል፡፡ ይኼ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡” ይላሉ በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ መነን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲሳይ ለማ፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር በመሆኗ ልማትን ለማምጣትና ደህንነቷን ለማስጠበቅ የባህር በር ያስፈልጋታል፡፡ ጥያቄውም ምላሽ እንዲያገኝ ሰላምን በማስቀደም መስራት እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡ መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው ከሰሩ የማይሳካ እቅድ ስለሌለ፤ ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ መንግስት መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ልማትን በማፋጠንና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ህዝቡም ጠንካራ ሀገር እንድትኖር ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ መስጠትና ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
“ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ የሆነችው በቅርብ ጊዜ ነው” የሚሉት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ነዋሪ የሆኑት አቶ መሀመድ አደም “ኢትዮጵያ ለወደብ የምትከፍለው ክፍያ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ወጪ ማስቀረት ቢቻል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ የህዝቡን ኑሮ ያሻሽላል፡፡ ‘የባህር በር ማጣታችን ጎድቶናል’ የሚሉት አቶ መሀመድ፣ የባህር በር ፍላጎታችን ምላሽ እንዲያገኝ ከመንግስትና ከህዝብ ስራ ይጠበቃል። ህዝቡ በዋናነት ጠንክሮ በመስራት፣ ለሚነዙ አሉባልታዎች ጆሮ ባለመስጠት፣ ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

የባህር በር ለኢትዮጵያ አስፈላጊና የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ማንሳታቸውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተገኘው ውጤት አመርቂ የሚባል እንደሆነ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ማሩ ያነሳሉ፡፡ “አጀንዳው በአጭር ጊዜ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ለኢትዮጵያ የባህር በር አስፈላጊ መሆኑን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚያግባባ ነው፡፡ አሁን ከሀገር አልፎ አጀንዳው የአፍሪካ ጉዳይ ሆኗል፡፡” ይላሉ፡፡
የሶማሊያ መንግስትና ሶማሊላንድ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ላይ ለመደራደር ያሳዩት ፍላጎት እንደ ድል ይቆጠራል፡፡ የፈረንሳይና የተለያዩ ሀገራት መንግስታት የባህር በር ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ የሰጡት ይሁንታ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ጉዳዩ የሀገር ሉዓላዊነት በመሆኑ ይህንን የሚከታተል ምክር ቤትና ባለሙያ እንዲቋቋም በማድረግ በየጊዜው የሚገኘውን ውጤት እየገመገሙ መሄድ እንደሚያስፈልግ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ ማሳካት የማይችሉት ነገር የለም፤ ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የዓድዋ ድል እና በቅርቡ የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጨባጭ ማሳያዎች እንደሆኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ቅጠል እየለቀሙ በመሸጥ የሚተርፍ ሳይኖራቸው ህይወታቸውን ከሚመሩት ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀብት፣ የብሔር፣ ጾታ፣ ዕድሜ፣ የአመለካከትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድባቸው ለህልውናቸው አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት እና በአንድነት በመቆም እውን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የዓድዋ ድልም በህዝብ ትብብርና አንድነት የተገኘ ነው፡፡ እነዚህ ድሎች ህዝብን ባለቤት ማድረግ ከተቻለ ወደፊት ከዚህም በላይ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚቻል ማሳያዎች እንደሆኑ የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር) ያነሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ ወደኋላ የሚል አይደለም፡፡ በሚገባ ጉዳዩን እንዲረዳ ከተደረገ ሁልጊዜ ከሀገሩ ጎን ለመቆም ዝግጁ እንደሆነ የሚያነሱት የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር)፣ “የባህር በር ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ መንግስትና ብሔራዊ የጦር ሀይል መኖር አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት መንግስት ህዝብን በማስተባበር ላይ መስራት ይኖርበታል፡፡ ህዝቡም ልማትና ሰላምን በማስቀደም በአንድነት መቆም አለበት፡፡ ህዝብን ማስተባበር ከተቻለ የባህር በር ጥያቄም ልክ እንደ የህዳሴ ግድብ ወደ እውነት ይቀየራል” ብለዋል፡፡
“የህዳሴ ግድብ እውነተኛ የህዝብ ባለቤትነት የታየበት ስራ ነው” በማለት ከላይ የተነሳውን ሀሳብ የሚያጠናክሩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ማሩ፣ የህዝብን አቅም መጠቀም ከተቻለ የባህር በር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ያብራራሉ፡፡
“ባለፉት ሰላሳና ከዚያ በላይ ዓመታት የባህር በር ጉዳይን ማንሳት የሚያሳፍርና የተረሳ ጉዳይም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ስለወደብ ምንነት የማያውቅ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡” የሚሉት አቶ ማሩ ጥያቄው የአንድ የፖለቲካ ፓርቲና መንግስት፣ የአጭር ጊዜ ሳይሆን የትውልድ ነው። ከዚህ አኳያ አስፈላጊነቱን በህዝብ ዘንድ ለማስረፅ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ፎረሞችን በመመስረት ከጎረቤትና የአፍሪካ ወንድም ህዝቦች ጋር መወያየት ይገባል፡፡ ወንድም ከሆኑ የጎረቤት ሀገራት ህዝቦች ሀሳቦቻቸውን እንዲያዋጡ፣ ባለሙያዎች እንዲገናኙና ምን የጋራ ጥቅም እንደሚገኝ ማስረዳት ያስፈልጋል።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ማሩ እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በጥቅም፣ በእውነት፣ በህግ በመነጋገር ላይ ሊሳካ የሚችል መሆኑን የዓለም ተሞክሮ ያሳያል፡፡ የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ እንደተመላከተው ኢትዮጵያ የባህር ባለቤት እንድትሆንና ለቀይ ባህር ካለን ቅርበት የተነሳ የሚደርሱብንን ስጋቶች ለመቀነስ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የውስጥ አቅምን ማጠናከር፣ የዜጎች የባህረኛነት ሙያና ባህል ማጎልበት፣ የትብብር እድሎችን መጠቀም፣ የብዝሃ ሀይል ዓለም አቀፍ ፖለቲካን መጠቀም፣ ቀጣናዊ ትስስርን ወደ ጠንካራ ኮንፌዴራላዊ ሕብረት ማሳደግ የሚሉና ሌሎች ስትራቴጂዎችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “የመደመር መንግስት” በተሰኘው መጽሐፋቸው በተመረቀበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የሚችል ነው፡፡ ‘ኢትዮጵያ የመልክዓ ምድር እስረኛ ሆና ለዘላለም ትኖራለች’ ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ መኖር እንደሌለበትም አንስተዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ