በአብርሃም ገብሬ
ደራሲ አዳም ረታ በልብ ወለዶቹ ውስጥ የኢትዮጵያን ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ማህበራዊ መስተጋብር እና የወል ዕሴቶችን በምልዓት ዳስሷል፡፡ የኢትዮጵያን ከፍታና ዝቅታ፤ የህዝቡን ደስታና እዝነት በውብ የአጻጻፍ ይትበሃል አስነብቦናል፡፡ ግለሰባዊነትን ከማህበራዊ ማንነት ጋር እያዛመደ ኑረታችንን ሂሷል፡፡
አዳም ረታ የመጀመሪያ አጫጭር ልብ ወለዶች ስብስብ ከሆነው ማህሌት̕ ድርሰት በ1981 ዓ.ም ካሳተመበት ጊዜ አንስቶ አፍ̕ የተሰኘው ስግር ልብ ወለድ እስካሳተመበት 2010 ዓ.ም ድረስ ስድስት አጫጭር እንዲሁም አራት ረዥም ልብ ወለዶችን ለተደራሲያን አብቅቷል፡፡
በእነዚህ ድርሰቶቹም ከፍ ያሉ ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎችንና ማህበራዊ ሂሶችን አስነብቦናል፡፡ በተለይ ታሪክ፣ ማህበረሰባዊ መስተጋብር፤ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን፣ የሰው ልጆችን የህልውና እና የዕጣ ፈንታ ጉዳዮችን በልብ ወለዶቹ ውስጥ በምልዓት ተዳስሷል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያዊ የሆኑ የወል ፍልስፍናዊ እሳቤዎችን አጉልቶ በማሳየት ረገድ አዳም ረታ ከፊተኛው ረድፍ ላይ የሚቀመጥ ደራሲ ነው፡፡
በተለይ ደራሲው ወደ በኋላ አካባቢ በታተሙ ስራዎቹ ውስጥ በኢትዮጵያዊ እይታዎች የተቃኙ ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎችን በስፋት አስተዋውቋል፡፡ በተለይም በ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’፣ በ ‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’፣ በ‘የስንብት ቀለማት’ እና በ‘አፍ’ ውስጥ እነዚህን ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎችና ማህበራዊ ሂሶች ጎልቶ የተንጸባረቀባቸው ልብ ወለዶች ናቸው፡፡ በዚህ አምድም ደራሲ አዳም ረታ በፈጠራ ድርሰቶቹ ውስጥ የወል ማንነት፣ ዕሴትና ሀገራዊ ተረክ ለመስራት ያደረገው ኪነ-ጥበባዊ ሃሰሳን በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡
ያልተሄደበት የደራሲው መንገድ
ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች በባህሪያቸው ሰዋዊ ናቸው፡፡ ህብራዊነትን እና አብሮነትን አጉልተው ያሳያሉ። ሰውን ዋነኛ ነገረ-ጉዳይ አድርገው ስለሚነሱ ተጽዕኗቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም የጥበብ ስራዎች ለሰው ልብ እጅግ የቀረቡ በመሆናቸው ተጽዕኗቸው በአንድ ማህበረሰብ ወይም አካባቢ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የተከየነበትን ባህል፣ ቋንቋና ዐውድ ሳይገባን ዕሴትን እንድንጋራ፣ የወል ማንነታችን እንዲጎለብት፣ የጋራ ትርክት እንዲፈጠር በማድረግ የጥበብ ሥራዎች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡
በዚህም ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እንደ እርሾ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ለጋራ ማንነት መጎልበት፣ ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር፣ የሀገር ፍቅርን ከፍ በማድረግ፣ የወል ትርክትን በመስራት እና ሂሳዊ አስተሳሰብን በማበረታታት ሚናቸው ትልቅ ነው። እንዲሁም የወል የሆኑትን ባህላዊ ቅርሶችን አጉልቶ በማሳየት፣ አንድነትን በማጎልበት፣ የሀገርን እሴቶች እና መሻቶችን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ የሆኑት ቴዎድሮስ ገብሬ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ባዘጋጀው አንድ መድረክ ላይ “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ ጥናት ላይ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንና የደራሲ አዳም ረታን ስራዎች በሀገራዊ ብሔርተኝነትና ሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ስላላቸው አስተዋፅኦ ነበር ትኩረት ያደረገው፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ እንደሰፈረው፣ ደራሲ አዳም ረታ “ለማንነትና ለሀገር ግንባታ ፕሮጀክት ማህበረሰቡን የሚያስተሳስሩ ጥቃቅን ነገሮችን በምልክትነት (በውክልና) ይወስዳል፡፡ ለአብነትም በብዙ ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የማይጠፋው እንጀራ (ጤፍ) የኢትዮጵያውያን የወል ማንነትና ትውስታ የሚተው ትልቅ ዕሴት ነው” ሲል በድርሰቶቹ ውስጥ አጉልቶ እንደሚያሳይ ምሁሩ ጽፈዋል፡፡
በእርግጥም “እንጀራ ይውጣልህ”፣ “ወፍራም እንጀራ ይስጥህ”…የሚሉ ምርቃቶች ማህበረሰቡን እንጀራ ከዕለት ተዕለት ምግብነት ባለፈ በተለዋጭ ዘይቤነት (metaphor) የሚጠቀመውም ለዚህ እንደሆነ የደራሲው ሥራዎች ጥሩ አስረጅ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የወል አስተሳሳሪ እሴቶችን የመለየትና የማጉላት ስራ በዚህ መልኩ በኪነ-ጥበብ ስራዎች አማካይነት እንደሚሰራ ደራሲ አዳም በድርሰቶቹ አሳይቷል፡፡
ጉርሻ ወይም መጎራረስ በሀገራችን ማህበረሰብ ውስጥ ጎልቶ የሚንጸባረቅ ልማድ ነው፡፡ ወዳጅነታችንን የምናሳየው በመጎራረስ ነው፡፡ እንግዳ ሆኖ የቀረበን ሰው እንግድነት እንዳይሰማው ለማድረግ ምግብ በማጉረስ ወዳጅ እናደርገዋለን። ይህ አይነቱ ልማድ በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች የተለመደ የጋራ ዕሴት ነው፡፡ ደራሲ አዳምም ጉርሻን ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ እሴት አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡
ለአብነትም በ2001 ዓ.ም በታተመው ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’ ድርሰቱ ውስጥ ስለ ጉርሻ ምንነትና በተለያዩ የሀገራችን ማህበረሰቦች ዘንድ በጉርሻ አማካይነት የቅርብ ወዳጅነትን እንዴት እንደሚያንጸባርቅ አሳይቷል፡፡ ደራሲ አዳም የጉርሻን ቅርጽ ከአክሱም ሃውልት ቅርጽ ጋር ጭምር አነጻጽሮ ጽፏል፡፡ እንዲሁም እንጀራ በተለያዩ የሀገራችን ማህበረሰቦች ዘንድ ለገበታ የሚቀርብ የዘወትር ምግብ መሆኑን በማተት፤ ይህም ማህበረሰቡን ካስተሳሰሩ ነባር ዕሴቶች መካከል አንዱ ነው ይላል፡፡
ደራሲና ሃያሲ ገዛኸኝ ድሪባ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን ባጋራው አስተያየት “በአዳም ረታ የአከያየን ዘይቤ እጅግ እገረማለሁ፡፡ በተለይ ለጥቃቅን ነገሮች ያለው መረዳት እጅግ ያስደንቃል። ብዙዎች ሊያስተውሉት የማይችለውን ደቃቅ ነገር እሱ ግን ሰፊ ቦታ ሰጥቶ ይተነትነዋል፡፡ እነዚህ ጥቃቅን ነገሮች እንዴት በጋራ እንዳስተሳሰሩንና የወል ማህበረሰባዊ ተረክ መሆን እንደሚችሉም በግልጽ አሳይቶናል” ሲል አጫውቶናል፡፡
ደራሲ አዳም እንደ ንድፈ ሃሳብ ያረቀቀው “ህጽናዊነት” የተሰኘው ንድፈ-ሃሳብም ዋነኛ ማጠንጠኛው እንጀራ ነው። እንጀራ የብዙ ኢትዮጵያውያን የዘወትር ምግብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ዘወትራዊ ምግብ የወል ልማድም ሆኗል። ደራሲው ከዚህም ተሻግሮ የኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ መስተጋብር በእንጀራ አይኖች ይመስላል። ማለትም በአንድ ክብ እንጀራ ላይ እርስ በእርሳቸው የተያያዙ በርካታ የእንጀራ አይኖች የማህበረሰቡ እርስ በእርስ መተሳሰር ማሳያ አድርጎ ያየዋል፡፡
ደራሲው ይህንን የእንጀራ አይኖችን በመጠቀም ነው ሥነ ጽሑፋዊ ንድፈ-ሃሳብን ያረቀቀው፡፡ እንደ ስንብት ቀለማትና መረቅ ያሉ እጅግ ተወዳጅ ድርሰቶች በዚህ የህጽናዊነት (የእንጀራ ኔትዎርካዊ ትስስር) ንድፈ-ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ከዚህ አንጻር ባህላዊ ምግቦቻችን ከዕለታዊ ምግብነት የተሻገረ ማህበረሰባዊ ፋይዳና ኪነ ጥበባዊ ሚና እንዳላቸው ደራሲው በስራዎቹ አጉልቶ ማሳየቱ፤ ለወል እሴቶቻችን ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለብን አመላካች ነው፡፡
እንደ ደራሲ ገዛኸኝ ገለጻ፣ አዳም ረታ በድርሰቶቹ ውስጥ “ኢትዮጵያዊ የሆኑ የወል ፍልስፍናዊ እሳቤዎችን ድንቅ በሆነ ኪናዊ አቀራረብ ከሽኖ አቅርቦልናል። የተውናቸውን፣ የዘነጋናቸውንና ችላ ያልናቸውን ሀገር በቀል ዕሴቶቻችንን ትልቅ ረብ እንዳላቸው አሳይቷል” ብሏል።
በ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’ ሰዓሊና ሃያሲ መስኮት ገረሱን፣ የዘመኑን ሁኔታ እንዲተነትን፣ እንዲሄስና እንዲፈክር በደራሲው የተቀረጸ ገጸ-ባህሪ ነው፡፡ ገጸ-ባህሪው መስኮት ገረሱ እንዲህ ይላል፤ “እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ አንዳንድ ቦታ እንጀራ በቢላ ሲቆረስ እናያለን፡፡ ይሄን በቢላ የመቁረስ ባህል የጀመረው ማን ነው? ለምን ጀመሩ? እንጀራን በቢላ መቁረስ እንጀራን ወደ ዳቦ ለማውረድ መጣር እንደሆነ አልተረዱም? የእኛ ትልቁ ችግራችን ዕውር ኮፒ አድራጊዎች መሆናችን ነው፡፡ ፈረንጅ ዳቦ ሲቆርስ አይተን ከዛ ያን በጭፍን ያለ ጥየቃ ያለ ትንታኔ ተበደርን፡፡ የዚህ ችግር መነሻው በራሳችን ማመን አለመቻላችን ነው። በራሱ የማያምን ሕዝብ ወደ ባርነት የሚጓዝ ነው…” (እቴሜቴ፣ 16) ይላል፡፡
የ‘እቴሜቴ ሎሚ ሽታ’ው መስኮት ገረሱ ሀገር በቀል ልምዶቻችንን ከማጉላት ይልቅ ከውጭ በጭፍን የሚኮረጁ ነገሮችን ነው የሚተቸው፡፡ በዚሁ ድርሰት ውስጥ መስኮት የተገፉትን የወል ሀገር በቀል እሴቶች ወደ መድረኩ እንዲመጡ ይተጋል፡፡ መስኮት በስዕል ስራዎቹና ለጋዜጦች በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች አማካኝነት ይህንን ሃሳቡን ያስተጋባል። ለአብነትም መስኮት አስቀድሞ ይከተለው የነበረውን አውሮፓዊ የ“አብስትራክት ኤክስፕረሽኒዝም” (Abstract expressionism) የአሳሳል ዘይቤ በመተው፣ የሀገር በቀል ዕውቀትና ልምድን መሰረት ያደረገ “ተነካናኪ” ወይም “ቅርባዊነት” የተሰኘ የአሳሳል ዘይቤ ፈጥሯል፡፡
ቅርባዊነትን (በእቴሜቴ፣15) መስኮት ሲያብራራው፤ “በሀገራችን የባህል አሳሳል የበላይነት ቦታ ያላቸውን ዐይንና ፊትን በተለይ ዐይንን በሌሎች የስሜት ሕዋሳትና ብልቶች ቀስ በቀስ መተካትና ቢቻል እኩል ለማድረግ የሚሞክር የአሳሳል ዘይቤ ነው፡፡ በባህል ስዕሎቻችን ዐይን ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ዐይን ማለት ርቀትና ሃሳባዊነት ሲሆን፣ የየቀኑ ኑሯችን ግን የቅርብ፣ አፋኣዊና ተነካናኪ ነው፤” በማለት ይቀጥላል፡፡ በአጠቃላይ በአዳም ስራዎች ውስጥ የወል ዕሴቶች ጎልተው ይነበባሉ፡፡ ዘወትር የምንመገባቸው እንደ እንጀራ ያሉ ምግቦችም የወል ትስታንና ተረክ እንደሚሰሩም ማሳየት ችሏል፡፡
በአጠቃላይ ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ወሳኝ መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ለጋራ ማንነት መጎልበት፣ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር፣ ሀገር፣ ፍቅርን ከፍ በማድረግ እና ሂሳዊ አስተሳሰብን በማበረታታት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። እንዲሁም የወል ባህላዊ እሴቶችን አጉልቶ በማሳየት፣ አንድነትን በማጎልበት የወል ታሪኮችና ልምዶችን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በዚህ በኩል የአዳም ረታ ድርሰቶች ለሌሎችም ከያኒያን መንገድ የሚያሳዩ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡