የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ የነገው መሠረት

You are currently viewing የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ የነገው መሠረት

የዘመናዊ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች መሥራች የሆኑት ባሮን ፒየር ደ ኩበርታን “ኦሎምፒክ የአካል፣ የአዕምሮ እና የፍላጎት ባሕርያትን በአንድ ሚዛናዊነት የሚያስተሳስር የሕይወት ፍልስፍና ነው” ብለውታል። ኦሎምፒክ ከሜዳሊያ ብዛት በላይ የሆነ፣ የዓለም ሕዝቦችን የሚያቀራርብና የሰላምን፣ የጓደኝነትን እና የፍትሐዊ ውድድር እሴቶችን የሚያንጸባርቅ እንቅስቃሴ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስፖርት ትኩረት ውስጥ ትልቅ ቦታ መያዝ የጀመረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታም በኦሎምፒክ መንፈስ መካሄድ የጀመረ አዲስ ምዕራፍ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ (ኢኦኮ) አዘጋጅነት የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር፣ የወደፊት የስፖርት ኮከቦችን ቀድሞ የመለየት እና የማዘጋጀት ዓብይ ዓላማ ያነገበ ነው።

ዓለም አቀፉ የወጣቶች ኦሎምፒክ ዓላማን መሠረት ያደረገው ይህ የሀገር ውስጥ መድረክ፣ በዋነኛነት እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት ባለው ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ያሳትፋል። ውድድሩ ለዓለም አቀፍ ደረጃ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ዕድል ከመስጠቱም ባሻገር፣ ስፖርት የሕይወት አካል እንዲሆን በማድረግ የኦሎምፒክ መንፈስ በወጣቱ ዘንድ እንዲሰርጽ ያደርጋል። እንደዚሁም ውድድሩ እንደ እግር ኳስ፣ ቮሊ ቦል፣ እጅ ኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ እና ቴኳንዶ ባሉ የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ላይ በማተኮር፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ያላትን የሜዳሊያ ምንጭ ለማስፋት ያለመ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ይገልጻል።

እስከ አሁን የተሄደበት መንገድ የሚያዋጣ አለመሆኑን የሚገልፁት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን በብዛት ማፍራት እንደሚያስፈለግ ይገልጻሉ፡፡ በመጪው ታህሳስ ወር በአንጎላ በሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች የሚካሄደው በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መርህ መሠረት ሆኖ፣ ሁሉም ተወዳዳሪዎች በአንድ መንደር (በተወሰነ አካባቢ) ሆነው ባህልና እሴቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዚህ መድረክ የሚታዩት ወጣቶች፣ ለቀጣይ የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች እና ለዳካር 2026 የወጣቶች ኦሎምፒክ እንደ መለኪያ እና መግቢያ በር ሆነው ያገለግላሉ። ለምሳሌ በሐዋሳው የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች፣ ለግብፅ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ተሳትፎ መሠረት መሆናቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት አሸብር ወልዴ ጊዮርጊስ (ደ/ር)  የውድድሩን ዓላማ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በሀገሪቱ ያሉ ወጣቶችን ዕድል በመስጠት ጥሩ ጥሩ ልጆችን ለመምረጥ ያስችላል። እንደዚሁም በቀጣይ በአንጎላ ለሚደረገው የአፋሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ እና የዛሬ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በምድረ አፍሪካ በሴኔጋል ዳካር ለሚካሄደው የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ያለመ እንደሆነም አብራርተዋል።

በአንደኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ከአራት ዓመት በፊት በሐዋሳ ከተማ የተሰናዳ ሲሆን ይህ ታሪካዊ ውድድር ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ወጣቶቻቸውን አዘጋጅተው እንዲቀርቡ በማድረግ የውድድር ስሜትን በሀገር ደረጃ ይበልጥ አነሳስቷል።

በሐዋሳው ውድድር የአዲስ አበባ ከተማ በሜዳሊያ ብዛት ከፍተኛ ደረጃ በመያዝ የውድድሩ የበላይ ሆና አጠናቅቃለች። ኦሮሚያ ክልል እና የደቡብ ክልልም ተከታይ ደረጃዎችን በመያዝ የክልሎችን የስፖርት አቅም አሳይተዋል። ይህ ውድድር በሀገሪቱ ውስጥ በትክክለኛ እድሜ ላይ የተመሠረተ የውድድር ሥርዓት አስፈላጊነትን በማጉላት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሁልጊዜም እንደሚያሳስበው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ዋናው ተግዳሮት እና ትኩረት የውድድሩን ፍትሐዊነት ማስጠበቅ ነው። በኢትዮጵያ የስፖርት ዘርፍ በተለያዩ ጊዜያት ችግር ሆኖ የቆየው የዕድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ለዚህ ጨዋታ ትልቅ ፈተና እየሆነ መጥቷል። ይህን ችግር ለመቅረፍ ኮሚቴው በዓለም አቀፍ መርህ መሠረት የኤም.አር.አይ (MRI) ምርመራን በመጠቀም የአትሌቶችን ትክክለኛ ዕድሜ የማረጋገጥ ሥራ እያከናወነ ነው። ይህ ጥብቅ ቁጥጥር ወጣቶቹ ተወዳዳሪዎች በትክክል በእድሜያቸው ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲወዳደሩ በማስቻል፣ ለዓለም አቀፍ መድረክ ሲሄዱ በዕድሜ ምክንያት ውድቅ እንዳይሆኑ ይከላከላል። የዕድሜ ማጭበርበር አባዜ ለማስቀረት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን ሰፊ ስራዎች እንደተከናወኑም ተነግሯል፡፡

የዓለም አቀፉ የወጣቶች ኦሎምፒክ ታሪክ ሲታይ፣ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ውጤቷ ቢታወቅም፣ እንደ ቴኳንዶ ባሉ ዘርፎችም ትልቅ አቅም ማሳየት መጀመሯ እምቅ ተሰጥኦዋን ያሳያል። በ2014ቱ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ላይ በቴኳንዶ 5 የወርቅ ሜዳልያዎችን ማግኘት መቻሉ፣ በትኩረት ከተሰራ በሌሎች ስፖርቶችም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተስፋ ሰጥቷል። የሀገር ውስጥ የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታም ለዚህ መስፋፋት ትልቅ መነሻ እንዲሆን ይነገራል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ዓላማው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ የሚገጥሙት ተግዳሮቶች ቀላል አይደሉም። ዋነኞቹ ችግሮች በቂና ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት መገልገያና ስታዲየም አለመኖር በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ የአፍሪካን ወጣቶች ኦሎምፒክ የማስተናገድ ዕድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም፣ በቂ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ምክንያት ዕድሉ መታጣቱ ይታወሳል። ይህ ሁኔታ የሀገር ውስጥ የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታም ያለበትን የመሠረተ ልማት ክፍተት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተናጋጅነት የሚካሄደውና እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 2ኛው የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡ የውድድር ሜዳዎች፣ የመለማመጃ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪ ስፖርተኞች የማደሪያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ተናግረዋል። ለ2ኛው የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች 15 የውድድር ሜዳዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና 16 የልምምድ ሜዳዎች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መረጃ መሰረት ውድድሩ 20 በሚደርሱ የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ ከ12 ክልሎች እና ከ2 የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል። በውድድሩ የቦክስ ስፖርት እንደማይኖር ሲገለፅ ለዚህም ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እውቅና የተሰጠው የቦክስ ፌዴሬሽን ባለመኖሩ ነው ተብሏል።

ከ4 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ በ2014 ዓመተ ምህረት በሐዋሳ ከተማ ተከናውኖ እንደነበር አይዘነጋም። የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በታህሳስ 2018 ዓ.ም በአንጎላ ይደረጋል። ውድድሩ ለወጣቶች ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የነገ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት መሆኑንም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገልጿል። እ.ኤ.አ በ2026 በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሴኔጋል ዳካር የሚካሄደው የወጣቶች ኦሎምፒክ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ዋነኛው ትኩረትም ለዚህ ታላቅ መድረክ ብቁ ወኪሎችን መምረጥ ነው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review