አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር ክሪስታል ፓላስን ይገጥማል

You are currently viewing አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር ክሪስታል ፓላስን ይገጥማል

AMN-ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል አርሰናል ከ ክሪስታል ፓላስ የሚያደርጉት ይጠበቃል።

የዛሬው ጨዋታ አርሰናል በተከታታይ የሚያደርገው ሦስተኛው የለንደን ደርቢ ይሆናል።

በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ዌስትሃም ዩናይትድ እና ፉልሃምን ያሸነፉት መድፈኞቹ ክሪስታል ፓላስን ያስተናግዳሉ።

ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው አርሰናል የመከላከል ጥንካሬው አስደናቂ ነው።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ በሊጉ ጥቂት ሙከራ የተደረገበት ቀዳሚው ክለብ እንደሆነ የኦፕታ ቁጥራዊ መረጃ ያሳያል።

ባለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች አርሰናልን የገጠሙ ክለቦች 65 ሙከራ ሲያደርጉ 18ቱ ብቻ ናቸው ኢላማቸውን የጠበቁት።

ኢላማቸውን ከጠበቁ ሙከራዎች ሦስቱ ብቻ ግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያን አልፈዋል።

በእነዚህ የመከላከል ቁጥሮች አርሰናል ጋር የሚጠጋ ሌላ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ የለም።

የሚካኤል አርቴታ ቡድን ግብ በማስቆጠርም አይታማም ፤ ከማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ በመቀጠል ሦስተኛው በርካታ ግብ ያስቆጠረ ክለብ ነው።

የቡድኑ ችግር ከክፍት ጨዋታ በርካታ ግቦችን አለማስቆጠር እንደሆነ ይታያል።

የሊጉ መሪ ከክፍት ጨዋታ ከሰንደርላንድ እና በርንሌይ ያነሰ አምስት ግብ ብቻ አስቆጥሯል።

ሌሎች በሊጉ ያስቆጠራቸው 10 ግቦች ከቆሙ ኳሶች የተገኙ ናቸው።

በተለይ ከማዕዘን ምት ማስቆጠር እንደ አርሰናል የቀለለው ክለብ የለም። በሊጉ ካስቆጠራቸው 15 ግቦች ሰባቱ የተገኙት ከማዕዘን ምት ነው።

አርሰናል ዛሬ የሚገጥመው ክሪስታል ፓላስ ቀላል ተጋጣሚ አይደለም።

ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ ባይሆንም የኦሊቨር ግላስነር ቡድን አሁንም አስፈሪ ነው።

ፓላስ ባደረጋቸው ስምንት የሊግ ጨዋታዎች 43 ኢላማቸውን የጠበቁ ሙኩራዎችን በማድረግ ከሁሉም ክለቦች ይቀድማሉ።

በዦን ፊሊፕ ማቴታ የሚመራው የአጥቂ ክፍል ትልቁ ድክመት ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ነው። ፓላሶች ከፈጠራቸው 33 ትልልቅ እድሎች 22ቱን ዋጋ ቢስ አድርገውታል።

አርሰናል ከ ፓላስ በመጨረሻ ስድስት ግንኙነታቸው አርሰናል አምስቱን በድል ተወጥቷል።

ጨዋታው ቀን 11 ሰዓት በኤምሬትስ ይከናወናል።

በተመሳሳይ ሰዓት አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ማንችስተር ሲቲን ሲያስተናግድ ፤ ቦርንማውዝ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት ይጫወታሉ።

ኤቨርተን እስካሁን ሽንፈት ባልቀመሰበት አዲሱ ስታዲየሙ ሂል ዲኪንሰን ቶተንሃም ሆትስፐርስን ምሽት 1:30 ያስተናግዳል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review