የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ አሁን ላይ እየተገነቡ ያሉ የትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ትልቅ እመርታ የታየበት በመሆኑ ለቀጣይ ሥራዎች ተሞክሮ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን አስመልክቶ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የመከላከያ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይሻ መሃመድ በራስ አቅም ሀገራዊ የሆኑ አስተሳሰቦችንና አሰራሮችን በመጠቀም በተሰሩ ስራዎች በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በማዕድንና በሌሎችም ዘርፎች አመርቂ ለውጥ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ከማቀድ በዘለለ በተግባር መፈጸም እንደሚቻል ለቀጣናው፣ ለአህጉርና ለአለም እያሳየን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የኢኮኖሚ እድገቱ : አሁን ያለው ትንበያም ሆነ በላፈው አመት የነበረው አፈፃፀም ሀገራዊ እድገቱን በእጅጉ የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለማዕድን ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ጨምሮ በስሚንቶ፣ ድንጋይ ከሰል፣ በብረትና በመሳሰሉት ማዕድናት ዘርፍ ላይ ውጤታማ ሥራ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የተቀረፁ ፖሊሲዎችና ሪፎርሞችን በአግባቡ በመተግበር ሀገሪቱን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ አሁን ላይ ግብርናውን አስከትሎ ኢንዱስትሪው የመሪነቱን ሚና መረከብ እየቻለ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በገጠራማ የሀገሪቱ ክፍሎች የተጀመሩና የተጠናቀቁ የኮርደር ልማት ስራዎች ከተሞችን ዘመናዊነት በማላበስ ለነዋሪዎች ምቹ መደረጋቸው አስደናቂ ለውጥ የታየበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰብዓዊ ድጋፍ ራስን ለመቻል በተሰጠው ትኩረት በክልሎች መካከል ያለው ትብብር የሚበረታታ ውጤት እየታየበት ነው ብለዋል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ