የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቢጠናቀቅም በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚደረጉ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አማባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል ።
አማባሳደሩ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ የተጠናቀቀ ቢሆንም በግድቡ ህልውናና ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እና የቀጣናውን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን በተመለከተ ከታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ጋር የሚደረጉ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራት አለባቸው ነው ያሉት።
በመንግስታት ከሚደረጉ ግንኙነቶች ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በታዋቂ ግለሰቦች፣ በአርቲስቶች እና በሚዲያ ሰፊ ስራ መሰራት እንደሚገባም ነው አምባሳደር ዲና የገለፁት።

አሁን ላይ የህዳሴ ግድብን ጠቀሜታ የማስረዳት ጉዳይ ላይ ሳይሆን ያለነው ሌላ ምዕራፍ ላይ ስለሆነ፤ በግድቡ የተገኘውን ተሞክሮ ለአፍሪካውያን፤ በተለይም ለታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ተልቅ ተሞክሮ መሆኑን የሚያመላክቱ ስራዎች መሰራት ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ በራስ ዓቅም ያስገኘው ውጤት ለሌሎች ሃገራትም ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ይህንንም ተሞክሮ የማስረዳት አና የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ነው ያሉት።
የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ በፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም በፀጥታ ጉዳይ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሩ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በመተግበር ሂደት በትብብር መስራት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።
በያለው ጌታነህ