ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለ4ኛ ጊዜ 1 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀመረ

You are currently viewing ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለ4ኛ ጊዜ 1 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀመረ

AMN – ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለ4ኛ ጊዜ 1 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ በማሰልጠን መንግስት የያዘውን ሰው ተኮር ፕሮጀክት እያፋጠነ መሆኑን አስመስክሯል።

በመዲናዋ በማህበራዊ ቀውስ ረዳት አጥተው በአስከፊ ህይወት ውስጥ የነበሩ ሴቶችን ወደ ተስፋ መንገድ በመውሰድ ለነገዋ ሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የታለመለትን ግብ ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል።

ማዕከሉ ከ3 ሺህ 500 በላይ ሴቶችን በ3 ምዕራፍ በተለያዩ የሙያ አይነቶች በማብቃት፣ በህይወት ክህሎት፣ በጤና እና ስነልቦና በመርዳት የተሻለ ህይወትን እንዲመሩ ሲሰራ ቆይቷል።

ዛሬም ለ4ኛ ጊዜ አንድ ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ በማሰልጠን መንግስት የያዘውን ሰው ተኮር ፕሮጀክት እያፋጠነ መሆኑን አስመስክሯል።

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሂርጳሳ ጫላ (ዶ/ር)፣ ከተቋሙ በሙያ ተመርቀው የወጡ ሴቶች ከፈተና ህይወት ተላቀው በኢኮኖሚ ራሳቸውን በመቻል የተረጋጋ ኑሮን እየመሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የመቀበል አቅምን በማሳደግ መጀመሪያ ከነበረው የ300 ሰልጣኞች ቁጥር ወደ 1 ሺህ ከፍ በማድረግ አዲስ የስልጠና ዘርፎችን በመጨመር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማዕከሉን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱም ወቅት፣ በከፋ ችግር ውስጥ ሆነው ህይወታቸውን ሲመሩ ለነበሩ ሴቶች ደራሽ የሆነ ትውልድንና ሀገርን የሚያኮራ ፕሮጀክት መሆኑን ዓባላቱ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።

የተቋሙ የተሟላ የስልጠና ዝግጅት ተወዳዳሪ፣ በሙያው የበቁ፣ በስነ-ልቦና የነቁ ሴቶችን ለማፍራት አስችሎታል ብለዋል።

የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ስኬታማ ስራ ማሳያ፣ ሰብዓዊ እና የተረሱ ወገኖችን ያስታወሰ በመሆኑ የአመራሩን ቁርጠኝነት ጥንካሬ ያሳየ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ተግባር ማየታቸውንም ገልጸዋል።

በአለኸኝ አዘነ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review