የሰራዊታችንን ፅኑ ጀግንነት የሚያሸንፍ ማንም ጠላት አልመጣም፣ አልታየም፤ወደፊትም አይመጣም ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ደህንነት የሚለካው በጦር ሜዳ በተገኙ ድሎች ብቻ ሳይሆን የመከላከያ ሰራዊታችን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ መስዋዕትነት ለመክፈል ባለው የማያቋርጥ ዝግጁነት መሆኑን ሚኒስትሯ የሃገር መከላከያ ቀን በተከበረበት ጊዜ ባደረጉት ንግግር አንስተዋል።
ይህ የዘወትር ዝግጁነትና ሀገር የመጠበቅ የማይታክት ፅናት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሰራዊታችን ላይ ያለውን ኩራት እና እምነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዋ፣ ለም መሬት እና የውሃ ሃብቷ እንዲሁም ታሪካዊ ቅርሶቿ እና ሌሎች ፀጋዎቿ ፤ ዕድል እና ተስፋ የሰፈነባት ሃገር ሆና እንድትኖር ቢያደርጋትም፤ ጠላቶቿ ሁልጊዜም ከዚህ ፀጋዋ እንዳትጠቀም ሊያሳንሷት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ሲሉ ነው የገለፁት።
ታዲያ ይህ ተግባር ዛሬም ድረስ በገሃድ የሚታይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይሁንና ክንደ ብርቱውንና ጀግና ሰራዊታችንን ከቆመበት ማማ ፈቀቅ ሊያደርጉት አይችሉም፤ ፈፅመውም አይቻላቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በየትውልዱ ማስጠበቅ የተቻለው በዚህ ቅብብሎሽ መሆኑን ያወሱት አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)፤ የጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ወኔና የምጊዜም ዝግጁነት ሉአላዊነታችንን ለመናድ የሚደረገውን ሴራ እያከሸፈ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና የምታመራበትን ጎዳና እየጠረገ ነው ብለዋል።
ነፃነቷን እና ክብሯን ለማስጠበቅ ህይወታቸውን መስዋእት የሚያደርጉላት እጅግ ውድ ሃገር አለችን ሲሉ ነው የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) የገለፁት።
በያለው ጌታነህ