6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ማካሄድ ጀምሯል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ከሰላምና ህግ ማስከበር ስራዎች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተደቀነባትን የህልዉና አደጋ በለዉጡ መንግስት በሳል አመራር መሻገሯን ያነሱን የምክር ቤቱ አባላት፣ አሁንም ድረስ ግን አንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች በህዝብና በመንግስት ትብብር ሊቀረፉ የሚገባቸዉ የሰላምና የጸጥታ ችግሮች መኖራቸዉን ጠቁመዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ካነሷቸዉም ጥያቄና አስተያየቶች መካከል፡-
በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ዛሬም ለሰላም መንገድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እንገነዘባለን ያሉት የምክር ቤቱ አባላት፣ በተለያዩ ክልሎች መንግስት ያቀረበዉን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ በርካቶች ወደ ቀዬአቸዉ በመመለስ ላይ መሆናቸዉ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም የመንግስትን ታጋሽነትና ሆደ ሰፊነት የሚያመላክት ተግባር ነዉ ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሕዝብንና የመንግስትን የሠላም ጥሪ ባለመቀበል ከኢትዮጵያ ቋሚ ጠላቶች ጋር በማበርና ተላላኪ በመሆን የባንዳንነት ተግባራቸዉን በመፈጸም የህዝብን ስቃይ ማራዘም የሚፈልጉና ኢትዮጵያን ለማዳከም ቀን ከሌት የሚሰሩ ጽንፈኛ ቡድኖች መኖራቸዉን አንስተዋል፡፡
እነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች ንፁሃንን ከማሰቃየትና ከመግደል ባለፈ መሰረተ ልማቶችን በማዉደም የህብረተሰቡን የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል ስለሚገኙ መንግስት በእነዚህ ቡድኖች ላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ምን አቅዷል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት የፖለቲካ ባህሉን ለመቀየር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት የመጠፋፋት ፖለቲካ፣ የብሽሽቅ፣ በስሜት የመጋለብ ፖለቲካ እንዲሁም እኛ እና እነሱ የሚል ከፋፋይና እጅግ ኋላ ቀር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ልምምድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ግጭትን በሃይል ለመቅረፍ ከመቻኮል ይልቅ፣ በታጋሽነትና በሆደ ሰፊነት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝና የእርቅና ሠላም መንገድን በመከተል የሃገሪቱን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑንም አንስተዋል፡፡
የዚህ ማሳያዉ የፕሪቶሪያዉ ስምምነትና በስምምነቱ የተገኙ ዉጤቶች መሆናቸዉን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ የፕሪቶሪያዉን የሠላም ስምምነት ወደ ጎን በመተዉ ከሃገሪቱ ህግና ስርዓት ባፈነገጠ መልኩ፣ በአዛዉንቶቹ የሚመራዉ የህወሃት ቡድን እና አንጃዉ ከጦርነት አዙሪት ዉስጥ ላለመዉጣት በሌሎች ክልሎችም ጽንፈኛ ቡድኖችን ጭምር በመጠቀምና ከኢትዮጵያ ቋሚ ጠላቶች ጋር በማበር ህዝቡን ዳግም ወደ ስቃይ ለማስገባት በየቀኑ የጦርነት ድግስ በማወጅ ላይ መሆናቸዉንም አንስተዋል፡፡
ጦር ሰባቂ ህገ ወጥ ቡድን አደብ ለማስገዛትና ጊዜአዊ አስተዳደሩን በማገዝ ክልሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል በመንግስት በኩል በታቀዱ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ የምክር ቤቱ አባላት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአዛዉንቶች የሚመራዉ የህወሃት ቡድን ከሻዕቢያ ሃይሎች ጋር ግንባር በመፍጠር ለጥፋት እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ መንግስት የቡድኖቹን እንቅስቃሴ መግታት እና የሃገር ሉአላዊነትን ማስከበር ይጠበቅበታል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ