አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ የሚደረግበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ የሚደረግበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ
  • Post category:ልማት

AMN ጥቅምት 18/2018

በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ የሚፈስበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

አየር ማረፊያው ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት አፍሪካን የማስተሳሰርና የማገናኘት መሻቷን በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ እየሰጡት ባለው ማብራሪያም በቢሾፍቱ የሚገነባው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የዲዛይን ስራ መጠናቀቁንና አማካሪ ድርጅት መቀጠሩን አመልክተዋል።

ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ አርሶ አደሮች ለልማት ስራቸውን ሲለቁ የሚስተናገዱበት መንገድ ችግር እንዳይሆን ኑራቸው እንዳይሰተጓጎልና አማራጭ የኑሮ ዘዬ እንዲከተሉ የተከናወነው ሰፊ ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን ለውጭ በረራ የምትጠቀመው የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መሆኑን ገልጸው አየር ማረፊያው በአዲስ አበባ ከመሆኑ አንጻር ያለበት ከፍተኛ ስፍራ አውሮፕላኖች ረዘም ያለ ጉዞ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ነዳጅ እንዳይዙ ማድረጉን ተናግረዋል።

አዲሱ አየር ማረፊያ የሚገነባበት ስፍራ አውሮፕላኖች በቂ ነዳጅ ይዘው ለመብረር ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

ግንባታው ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግድ መሆኑ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ እንደሚያደርገውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ በአየር ትራንስፖርት ውስጥ የአፍሪካ ማዕከል ሆና ከተቀረው የአህጉሪቱ ክፍል ጋር የማስተሳሰር እና የማገናኘት መሻት በእጅጉ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

ከለውጡ በኋላ በርካታ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የማስፋፊያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው አየር ማረፊያው ከ20 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ ቢችልም ከዛ አቅም በላይ መሻገር እንደማይችል ገልጸዋል።

አዲሱ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ፣ ኢትዮጵያን ከዓለም የሚያገናኝና ለአፍሪካ ብስራት የሚሆን ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review