በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሜጋ ኘሮጀክቶች በተሰጠው ትኩረት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ በተጨማሪ 14 መካከለኛና ከፍተኛ ግድቦች በ2ዐዐ ቢሊዮን ብር ወጪ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በ1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ወጪ 346 የመንገድ ኘሮጀክቶች በፌደራል መንግስት ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ሥራም 11ዐ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የመብራት ማስፋፊያ ኘሮጀክት ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲል የተጀመሩ የስኳር ፋብሪካዎች በአካባቢያቸው በቂ ግብዓት ሳይኖር የተገነቡ በመሆናቸው ውጤታማ መሆን አለመቻላቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በሚመለከተው አካል ታይተውና ተፈትሸው ማስተካከያ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በኘሮጀክት አፈፃፀም ረገድ የወርቅ ምርትን ጨምሮ ሌሎች ኘሮጀክቶችን ለማልማት ፈቃድ የሚወስዱ አልሚዎች በተፈለገው ልክ ወደ ስራ አለመግባታቸው እንዲሁም የኘሮጀክቶቹ ስፋትና ብዛት በተሟላ መልኩ ለመተግበር አዳጋች መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ በዘርፉ የተሟላ ሥራ ለመስራት መንግስት፣ ባለሀብቱና ህብረተሰቡ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እንዲሁም የተገለኙ ድክመቶች በመለየት በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው