ለአረጋዊያን ምቹ የመኖሪያ ከባቢን በመፍጠር እና የጤና ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ተኛ ጊዜ የአረጋውያንን ቀን “ለአረጋውያን ደሕንነትና መብት መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ ሃሳብ በ26ተኛው ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል አክብሯል።
በመር ሃግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ቅጣው፤ ለአረጋውያን ደህንነትና መብት መከበር የከተማ አስተዳደሩ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአረጋውያን ትኩረት በመስጠት በጤና መድን፣ በሴፍቲኔት፣ በቤት እድሳት፣ በምገባ መርሃ ግብር እና በተለያዩ ስራ እድል አማራጮች ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ አያይዘውም፣ ከተማ አስተዳደሩ የአረጋውያን ቅድሚያ ፍላጎቶች የሆኑትን ምቹ የመኖሪያ ከባቢን በመፍጠር እና የጤና ተቋማትን ተደራሽነት በማስፋት የአረጋውያንን ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አረጋውያን ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ፤ አረጋውያን ዛሬ ላይ ከተሳታፊነት ባለፈ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎችም አረጋዊያንን ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ታሪክን፣ ባሕልን እና በሕይወት ተሞክሮ የተገኙ እውቀቶችን ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹነትን ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
በመር ሃግብሩ ላይ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮው በሚሰጣቸው ድጋፎች ተጠቅመው ውጤታማ ለሆኑ አረጋውያን የማበረታቻ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
በታምሩ ደምሴ