ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉ ጥረቶች በየትኛውም መመዘኛ ቅቡል አይደሉም ሲሉ ምሁራን ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉ ጥረቶች በየትኛውም መመዘኛ ቅቡል አይደሉም ሲሉ ምሁራን ገለጹ

AMN ጥቅምት 20/2018

ኢትዮጵያን ያህል ታሪካዊ፣ ትልቅና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ሀገር የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉ ሂደቶች ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቅቡልነት እንደሌላቸው ምሁራን ገለጹ።

ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌትዬ ትርፌ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት በታሪካዊ ዳራ፣ ሕጋዊ ሠነዶች፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያነት ቅቡል እና አሳማኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በብዙ መመዘኛዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዳለው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው፥ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ያለውን የባሕር በር ለማግኘት ኢትዮጵያ ያነሳችው ጥያቄ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳለው ጠቅሰው ተገቢነቱንም አንስተዋል።

መንግሥት እየሄደበት ያለውን ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ አድንቀው፤ ኢትዮጵያን ያህል ታሪካዊ፣ ትልቅ እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ሀገር የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉ ሂደቶች ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቅቡልነት እንደሌላቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት ምክንያት አሳማኝና ተፈጥሯዊ ሳይሆን የሆኑ አካላት ሴራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር፣ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተመራማሪና ደራሲ ዳዊት መዝገበ ናቸው።

ሀገራዊ ብሎም ቀጣናዊ ትስስርን ከማጠናከር አኳያ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረግ ጥረት የአንድ ፓርቲ እና መንግሥት ፍላጎት ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት በማመን ጥረቶች መጀመሯ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሕዝቦች ትስስር፣ ከሀገር አልፎ ለቀጣናዊ ትብብር እና በጋራ ለማደግ የባሕር በር ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

ጥረቱን ለማሳካት ሰላማዊ ዲፕሎማሲ ማካሄድ ይመከራል ያሉት ምሁራኑ፥የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለቀጣናው ከሚኖረው ፋይዳ፣ የጋራ ዕድገትና ልማት አንጻር ሀገራት ቢተባበሩ እንደሚያተርፉ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሕጋዊ መሠረት፣ታሪካዊ እና የሠነድ ማስረጃ በአግባቡ ሠድራ በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ልዕልና ስልት ጥረቷን በይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንደሚጠበቅባትም መክረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ-ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን እናምናለን፤ የኅልውና ጉዳይ ስለሆነ ኢትዮጵያም ተዘግቶባት መኖር አትችልም ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review