ሩስያ በኒውክሌር ኃይል የሚሰራ በባህር ውስጥ የሚጓዝ ከፍተኛ ሱናሚ መቀስቀስ የሚያስችል አቅም ያለው ድሮን ላይ የተሳካ ሙከራ አድርጋለች።
“ፖሳይደን” ከተባለ ከጥንታዊ ግሪክ ከተወሰደ ቃል ስያሜ የተሰጠው ድሮኑ፤ በፍጥነቱ እና በጥልቅ ባህር ውስጥ በመጓዝ አቅሙ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሰርጓጅ መርከቦች ተወዳዳሪ እንደማይገኝለት ተነግሯል።
በድሮን ሙከራ መርሀግብሩ ላይ ታድመው የነበሩት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቴክኖሎጂው በባህር ዳርቻዎች ላይ ለሚደረጉ ውጊያዎች እጅግ ተመራጭ መሆኑን እና ኒውክሌር የመሸከም አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
ከ2018 ጀምሮ በምርምር ላይ የነበረው እና አሁን ስኬታማ መሆን የቻለው ድሮን፤ 20 ሜትር ርዝመት እና 100 ቶን ክብደት እንዳለው አርቲ አስነብቧል።
ከዚህ ባለፈም በ1 ሺህ ሜትር ጥልቀት በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር የመምዘግዘግ አቅም እንዳለውም ተነግሮለታል።
ሩስያ ይህን ኒውክሌር ማስወንጨፍ የሚችል የባህር ውስጥ ድሮን በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን ተከትሎ፤ በእስያ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለመከላከያ ሚኒስቴራቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ እ.ኤ.አ ከ1992 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፔንታጎን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቹን እንዲፈትሽ እና ሙከራዎችን እንዲያደርግ ነው ትዕዛዝ የሰጡት።
ሮይተርስ ባወጣው ዘገባ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፉክክር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን ጠቅሷል።
ከጦር መሳሪያ እና ከደህንነት ተንታኞች ባሰባሰበው መረጃም አዲሱ የሩስያ የባህር ውስጥ ድሮን የባሕር ላይ ውጊያ መልክን የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል።
በዳዊት በሪሁን