ግንባታቸው የተጀመሩ ግዙፍ ኘሮጀክቶች ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የነበሩ የኢኮኖሚ ስብራቶችን እና የማክሮ ኢኮኖሚ ዝንፈትን በማቃናት ውጤታማ እና ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጡ መሆናቸው ተገለፀ፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዮሐንስ በቀለ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በለውጡ መባቻ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስና የማክሮ ኢኮኖሚ ዝንፈት ውስጥ በመግባቷ ሀገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚው በድህነት አዙሪት ውስጥ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ይህም ከዕዳ ጫና፣ ከውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አለመኖር፣ ከምርታማነት ችግር እና ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ ሀገሪቱን ወደ ከፋ ድህነት ከቷት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
መንግስት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢኮኖሚ ስብራቱን በማቃናት ዘላቂ እና ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰዱን አመላክተዋል፡፡

ግንባታው የተጠናቀቀው የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና ሌሎች ግንባታቸው የተጀመሩ ሜጋ ኘሮጀክቶች የፖሊሲው ውጤት ሲሆኑ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ እንደ ሀገር ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኘሮጀክቶቹ ተመጋጋቢነት ያላቸው በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ወጪን በማስቀረት፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በማድረግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አቶ ዮሐንስ ገልፀው ሀገሪቱ ወደ ብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አቅምን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
እነኚህ ግዙፍ ኘሮጀክቶች በራስ አቅም በሀገር ውስጥ የሚሰሩ በመሆናቸው የዓለም ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን በመቋቋም እና ምላሽ በመስጠት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደሚያግዙ ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የገለጹት።
እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ አፍሪካን በልማት ለማስተሳሰር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ በቀለ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ያብራሩት፡፡
በበረከት ጌታቸው
 
								 
															 
 
							 
							