የኮሪደር ልማት የትውልድ ስነ ልቦና ስብራትን እያረቀ ያለ ስራ መሆኑ ተመላከቷል
ታዋቂዋ የከተማ ልማት ባለሙያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ማሪቼላ ሴፔ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በእስያ ከተሞች ላይ ያደረጉትን ጥናት ዋቢ በማድረግ እ.ኤ.አ ጥቅምት 10 ቀን 2022 ጤናማ እና ለኑሮ ምቹ ከተሞችን መንደፍ (Designing Healthy and Liveable Cities) የተሰኘ ጥናታዊ መፅሐፍ አሳትመዋል፡፡
ፕሮፌሰሯ በመፅሐፋቸው እንዳስቀመጡት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የከተሜነት መለኪያ የተደራረቡ የሕንፃ ጫካዎች ክምችት አይደለም። ይልቅ ከሰው ልጆች ነፍስና ስጋ ጋር የተወዳጁ፣ አምራችና ጤናማ መሆንን የሚያበረታቱ የመሆናቸው ምስጢር ነው የከተሜነት ከፍታው፡፡
በመሆኑም ባለንበት ዘመን ከተማ መገንባት ማለት በቀላሉ የሚታይ እሳቤ አይደለም፡፡ ለአብነትም ከተማ ስንገነባ የኮሪደር ልማትን ማሰብ ግድ ይላል፡፡ የኮሪደር ልማት ማለት ደግሞ ትራንስፖርትን፣ የሕዝብ መናፈሻ ቦታን፣ መዝናኛን፣ መኖሪያ ቤትን፣ ንግድን እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያዋህዱ ባለብዙ ተግባር ዞኖችን ማቀድን የሚያካትት ነው፡፡ በመሆኑም የኮሪደር ልማት ጤናማ፣ ንቁ እና ውጤታማ ትውልድን ለማሳደግ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ይላሉ የከተማ ልማት ባለሙያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ማሪቼላ ሴፔ፡፡
አዲስ አበባ ከተማም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘመን ብዛት የተጎሳቆለ መልኳን በልማት ወዝ አድምቃ እና የወየበ ልብሷን እንደ በረዶ አንፅታ፣ እርጅናዋን እንደ ንስር አድሳ፣ እንደ ጥቅምት አበባን ለብሳ፣ ደግሞም ጥር በሰርግ እንደሚደምቅ እሷም በኮሪደር ልማት ተውባ ትታያለች። ይህ ውበቷ ደግሞ ብዙ ትርጉሞች አሉት። ለአብነትም ባሳለፍነው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ ያነሱትን ሀሳብ እንጥቀስ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ አሉ “የኮሪደር ልማት የቦታና ጊዜ ምልከታን የሚቀይር ነው። ለአብነትም በአዲስ አበባ ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ተገንብቷል። በርካታ ወጣቶች ወደ ስፖርት እየተመለሱ ነው። ይህም ማህበረሰብን የመገንባት ስራ ነው። የትውልድ ስነ ልቦና ስብራትን እያራቀ ያለ ስራም ጭምር ነው። ይህን ማንም ሰው የሚያየው፤ ማንም ሰው የሚናገረው ጉዳይ ነው።”
በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ከተጎሳቆለ ኑሮና አካባቢ መውጣት የቻሉ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ለዚህ ምስክር ናቸው። ለአብነትም ወይዘሮ ሮማን ጌታቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ በተለምዶ ዶሮ ማነቂያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለ40 ዓመታት ኖረዋል፡፡ ትዳር ይዘው ልጆች ወልደው በኖሩበት መንደር ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ቢኖርም መታጠቢያ ቤት፣ መፀዳጃ ቤትም ሆነ በቂ የማብሰያ ክፍል እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ።
የሚኖሩበት ቤት ለስሙ ቤት ቢባልም የቤትነት መስፈርትን ያላሟላ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በአንዲት ጠባብ ክፍል ቤት ስምንት የሚሆኑ የቤተሰብ አባላት ልክ እንደዶሮ ቆጥ ላይ እያደሩ በስቃይ ኑሮን ሲገፉ ቆይተዋል፡፡ ይህ የትናንቷ ዶሮ ማነቂያ ሰፈር ውስጥ የነበረ የብዙዎች የኑሮ መልክ ነው፡፡
ከ15 የማያንሱ አባወራዎች በጋራ የሚጠቀሙት መፀዳጃ ቤትም ቢሆን አብዛኛው ተጠቃሚ ለማፅዳት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከአጠቃቀም ችግር ጋር ተዳምሮ ተጨማሪ የጤና ስጋት ይፈጥርባቸው ነበር፡፡ ክረምት ሲመጣ ደግሞ ችግሩ ከፍ ይል እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ሮማን፣ አሁን በኮሪደር ልማት የተሰጣቸው ምትክ ቤት ግን የተሻለ የመኝታ፣ ሳሎን፣ መፀዳጃና መታጠቢያ ክፍሎችን ጨምሮ ደረጃውን የጠበቀ መውጫና መግቢያ ያለው በመሆኑ የሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ጤና ጠብቀው ለመኖር እንደሚያስችላቸው መስክረዋል፡፡
የሰው ልጅ ስጋና መንፈሱ፣ ቤቱና መንደሩ፣ ውሎና አዳሩ ምቹ ከሆኑለት ምርትና ምርታማነቱ መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ከተሞች ከዘመኑ ጋር ሲወዳጁ ምንዳቸው ከፍ ይላል፡፡ ምክንያቱም ከተሞች የሀገራት ልብ ምት፣ የስልጣኔ መግቢያ በር፣ የምጣኔ ሀብት ርካብ፣ ቀን ነፍስና ስጋን ማስደሰቻ፣ ማታ ደግሞ ጨለማውን መርቻ የድል መቅረዝ ናቸው፡፡
የከተማ ኑሮ መሻሻል ምርታማነትን፣ ባህልን እና የሰው ልጆችን ደስታ ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት በከተሞች ኢኮኖሚና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን እና መፅሐፍትን ያሳተሙት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር እ.ኤ.አ በጥር 31 ቀን 2012 ‘ትሩምፊ ኦፍ ዘ ሲቲ’ (Triumph of the City) በተሰኘው ጥናታዊ መፅሐፋቸው ገልፀውታል፡፡
በጂማ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጤና ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ክፍል ፕሮፌሰር ሰይድ ትኩ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በተለይም ከህብረተሰቡ ጤና ጋር የሚያያዘ እንደ “ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” ባሉ ንቅናቄዎች በከተማዋ የተሰሩ ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶች ጤናማና አምራች ትውልድን ለመገንባት ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጎዳና ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የንፅህና ጉድለት አንዱ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ ክብር ያለው የንጽህና ባህል እና የተቀናጀ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓት መፍጠር ባለመቻላችን ምክንያት በማህበረሰቡ ጤና ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደሚፈጠሩ የገለፁት ፕሮፌሰር ሰይድ፣ ለአብነትም የመተንፈሻ አካላት ችግር አንዱ ነው። ይሄውም በደረቅም ሆነ በሌሎቹም ቆሻሻዎች ምክንያት የሚፈጠረው ብናኝ አየሩን በመበከል ወደሰዎች የመተንፈሻ አካል በቀላሉ በመግባት ከፍተኛ የጤና ችግር እያስከተለ መሆኑን እና በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያግዝ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
አክለውም በቆሻሻ ዙሪያ መቀመጥ፣ ማለፍም ሆነ ማሰብ ጤናን ብቻ ሳይሆን ምቾትንም ይነሳል፡፡ ይህም በከተሞቻችን በስፋት የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ ይህም የቆሻሻ አወጋገድ ባህላችን አለመዘመኑ፣ መንገዶቻችን ባለመስፋታቸውና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ታሳቢ አድርገው ባለመሰራታቸው የመጣ ነው፡፡ ይህም ክፍተት ከማህበረሰቡ ጤና መጓደል ጋር ትልቅ ትስስር አለው ብለዋል፡፡
የከተማ ንፅህና አጠባበቅ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር አስመልክቶ የተለያዩ ጥናቶችን እንዳደረጉ የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ በግኝቱም የመፀዳጃ ቤት በበቂ መጠን አለመኖር፣ ባሉትም በአግባቡ ያለመጠቀምና የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችን ባለመዘመኑ ምክንያት በማህበረሰቡ ላይ የተለያዩ ችግሮች እየተከሰቱ ነው፡፡
ለአብነትም በምግብ ሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋለውን ችግር የጠቀሱት ፕሮፌሰር ሰይድ፣ በተለያዩ ከተሞች በተደረጉት ጥናቶችም በቆሻሻ ስፍራ እና ባልታከመ ውሃ የሚያድጉ እንደ ቲማቲም፣ ቆስጣ፣ ጎመንና መሰል አትክልቶች ከፍተኛ የሆነ የበሽታ አምጭ ህዋሳት ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ አሁን እንደ ሀገር የተጀመረው የኮሪደር ልማት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን ለውጥ በአብነት አንስተዋል፡፡
በርግጥም አዲስ አበባ ከስምና ክብሯ ጋር በሚመጥን የልማት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ብዙዎች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡ ዕድሜና ወዝ፤ ለዛና ደርዝ ያላት ይህች ከተማ በረዣዥም ሕንፃዎች ጥግ የተጠለሉ ደሳሳ ጎጆዎች፣ በአንድ በኩል ምቹ በሌላው ደግሞ ለኑሮ አስቸጋሪ የሆኑ መሰናክሎች የበዙባትም ከተማ እንደነበረች ተደጋግሞ ተዘግቧል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ጉራማይሌነት ልክና መልክ ባለው መልኩ በመለወጥ በርግጥም ከተማዋ ‘አበባ’ ትመስል ዘንድ በርካታ ልማቶች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ከከተማዋ ውበትና ዝመና ባሻገርም የብዙ ወጣቶች ችግር የሆነውን የስራ ባህል ዝንፈት ማስተካከል የሚችሉ ተጨባጭ ማስተማሪያ የሚሆኑ ልማቶችንና ሰራተኞችንም በቅርብ ጊዜ ማፍራት እንደተቻለም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አሁን አዲስ አበባ ቀንም ሌሊትም የሚሰራባት ከተማ ሆናለች። ይህ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ የከፈተው አዲስ በር ነው፡፡
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) ከተማን ማዘመን (ስማርት ማድረግ) ያለንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ያግዛል፡፡ ከተማን ስማርት ማድረግ የመሰረተ ልማት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ይረዳል፡፡ መሬትን ምጣኔ ሀብታዊ አዋጭነት መሰረት ባደረገ መልኩ በአግባቡ ለመጠቀም ያግዛል፡፡ ይህ ደግሞ ያለንን ውስን የመሬት ሀብት ለተለያዩ ዘርፎች ማካፈል እንድንችል ይረዳል፡፡
በተጨማሪም፣ ለማህበረሰቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ እና በፍጥነት ለመስጠት ያግዛል፣ የሀገርን ገፅታ ያማረና የተዋበ በማድረግ ዓለም ዓቀፍ እይታን ይስባል፡፡ ይህም በቱሪዝም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ያለውን እንቅስቃሴ ያሳድግል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው በኮሪደር ልማትም ሆነ በሌሎች ተግባራት አዲስ አበባን ስማርት ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ጤናማና አምራች ማህበረሰብን ለመገንባት የሚያግዙ በመሆናቸው በምጣኔ ሀብት እሳቤ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ