”በሩብ ዓመቱ ለ96 ሺህ 210 ዜጎች ቋሚ  የስራ ዕድል ፈጥሬአለሁ”

You are currently viewing ”በሩብ ዓመቱ ለ96 ሺህ 210 ዜጎች ቋሚ  የስራ ዕድል ፈጥሬአለሁ”

የአዲስ አበባ ስራና  ክህሎት  ቢሮ

የተፈጠረው  የሥራ  ዕድል  ከታቀደው  የ18 ሺህ  710  ብልጫ  አለው

በመንግስት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ሀገራዊ አጀንዳዎች መካከል ለዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንንም መሰረት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያለውን ፀጋ በመጠቀም ለመዲናዋ ሥራአጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ በተያዘው የ2018 በጀት ዓመትም ለ350 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን ከአዲስ  አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ የሰጡት በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን እንደገለፁት፤ ለዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የቢሮው ዋና ተልዕኮ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በበጀት ዓመቱ ለ350 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግም ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት ተደርጎበታል፡፡

“ከሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች መካከል 75 ከመቶ የሚሆኑት ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የሴቶች ተጠቃሚነት ደግሞ 50 ከመቶ ይይዛል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ድርሻ 15 ከመቶ ለማድረግ ታቅዷል” ያሉት አቶ ሰብሃዲን፤ ከአጠቃላዩ የሥራ ዕድል መካከል 70 ከመቶው በቅጥር እንዲሁም 30 ከመቶ በማደራጀት የሚፈጠር እንዲሆነ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተያዙ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅዶች መካከል በዘርፍ ደረጃ ያለችውን ድርሻ በተመለከተ በአገልግሎት 58 ከመቶ፣ በኢንዱስትሪ 31 ከመቶ እንዲሁም በከተማ ግብርና 11 ከመቶ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አዲስ አበባ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችላት ፀጋ ያላት መሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ “ከተማዋ ቀንና ሌሊት ሠርቶ ለመለወጥ ለሚፈልግ ዜጋ በርካታ የሥራ አማራጮች አሏት” በማለት ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ያደረጉት ንግግር አስረጅ ነው፡፡ በመዲናዋ ያለማቋረጥ የሚከናወኑ የግንባታ፣ የአገልግሎት፣ የንግድ፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች መስኮች ለሥራ ራሱን ላዘጋጀ ዜጋ በርካታ የሥራ አማራጮች መሆናቸውን ለመረዳት ከልብ የመነጨ የሥራ ፍላጎት እና ሥራን ሳያማርጡ የመሥራት ቁርጠኝነትን ብቻ ይዞ መንቀሳቀስ በቂ ነው፡፡ ያኔ ሥራና ሠራተኛው በቀላሉ ይገናኛሉ፡፡

እንደ ከተማ አስተዳዳር ለዜጎች በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ፀጋዎች ስለመኖራቸው የሚስማሙት የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን እንደገለጹት፤ እያንዳንዱ ተቋም የሥራ ዕድል መፍጠርን ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ እንዲንቀሳቀስ ከፍተኛ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ተጨባጭ ውጤት በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር በሚያስችሉ ተቋማት (የመንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶች፣ የግል ተቋማት፣ ኢንተርፕራይዞች፣ ኢንዱስትሪዎች) በጥናት ላይ የተመሰረተ ፀጋዎችን የመለየት ሥራ ተከናውኗል። በዚህም 195 ሺህ 27 የሚደርሱ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚችሉ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ፀጋዎች ‘ምን ያክሉ ወደ ውጤት ተቀየሩ?‘ በሚለው እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንደ ተቋም በየ15 ቀኑ እንዲሁም በየወሩ በከተማ ደረጃ በተዋቀረ አብይ ከሚቴ አማካኝነት እየተገመገመ በመመራት ላይ ይገኛል፡፡

አክለው እንዳብራሩት፤ በከተማዋ ያሉ የመንግስት ተቋማት የሥራ ዕድል ፈጠራን አንድ አጀንዳቸው አድርገው እንዲሠሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እያንዳንዱ ጊዜ በተጨባጭ ውጤት በሚለካ ተግባር የሚያልፍ እንዲሆን ትኩረት ተደርጓል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከዚህ ቀደም የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት እና ሦስት ወራት የዝግጅት ምዕራፍ ተደርገው የሚወሰዱበት ልምድ ተቀይሮ በተሠራው ሥራ ከዕቅዱ አንፃር ከፍተኛ ብልጫ ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለው፡፡ ለማሳያነት ብንመለከት፤ በተያዘው 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እንደ ከተማ አስተዳደር ለመፍጠር የታቀደው የሥራ ዕድል 77 ሺህ 500 ሲሆን፤ ለ96 ሺህ 210  ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል 10 በመቶ አዳዲስ ምሩቃንን እንዲሁም 56 በመቶ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚተዳደሩ የመንግስት ተቋማት ለዜጎች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው በጥናት መረጋገጡን አቶ ሰብሃዲን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን አስመልክቶ እንዳስረዱት፤ በከተማ አስተዳደሩ ባሉ የመንግስት ተቋማት ብቻ ያለው አቅም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ በአስተዳደሩ ስር ከሚገኙ ተቋማት መካከል 18 ተቋማት ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር የተሻለ አቅም እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡ ከተቋማቱ መካከል የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ጋር የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በዚህም በተቋማቱ አማካኝነት በዚህ ሩብ ዓመት ብቻ ለ22 ሺህ 913 ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አጋዥ የሆኑ የመሥሪያ ቦታ እና የብድር አገልግሎት ከሚያመቻቹ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም እየተሠራ ይገኛል፡፡ 

ሥራ ፈላጊዎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊ ስልጠና፣ የመሥሪያ ቦታ እና የገንዘብ ብድር እንደሚመቻችላቸው አቶ ሰብሀዲን ገልፀዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ዜጎች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ባሉ 14 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ውስጥ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ኮሌጆች ባላቸው የሠው ኃይል፣ የስልጠና ሰነድ እና ግብዓት ለሰልጣኞች አስፈላጊውን ስልጠና የሚሰጡ ናቸው፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውስጥ በእነዚህ ኮሌጆች አማካኝነት ለ34 ሺህ 976 ዜጎች ከአምስት ቀን እስከ ሦስት ወራት የፈጁ ቴክኒካል ስልጠናዎች ተሰጥቷል። ከዚህ በተጓዳኝ የቴክኒካል ሰልጠና የወሰዱትን በሲኦሲ ምዘና የማብቃት ሥራ ተከናውኗል፡፡ ስልጠናዎቹም የዜጎችን እና የገበያውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው” ብለዋል፡፡

ከመሥሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ለ1 ሺህ 57 አዳዲስ ሥራ ለተፈጠረላቸው እና በሥራ ላይ ላሉ በማስፋፊያ የመሥሪያ ቦታ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር አምራቾችን በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች እና ሁነቶች እንዲሳተፉ በማድረግ በተሰራው ስራ ሁለት ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩን ከሥራና ክህሎት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ብድር አቅርቦትን በተመለከተ ከስኬት ባንክ ጋር ከተማ አስተዳደሩ በትብብር እየሠራ ነው፡፡ 

ቢሮው በከተማዋ ያሉ ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ጋር ለማገናኘት፣ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ፣ በዘርፉም ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሠጣጥን ተግባራዊ አድርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ለአገልግሎት የበቃው ቴክኖሎጂ “ጆብ ማናጅመንት ሲስተም (Job Management System-JMS)” የተባለ ሶፍትዌር ነው፡፡ ይህ ሶፍትዌር ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዙ እያንዳንዱን ተግባር በመረጃ ላይ ተመስርቶ ለመፈፀም አስችሏል። የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች (የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ነዋሪ፣ ሥራ አጥ፣ የሠለጠኑ መሆናቸውን) ለመመዝገብ እና መረጃ ላይ ተመስርቶ ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡ ተፈጠረ የተባለው የሥራ ዕድል ሊታይና ሊጨበጥ የሚችል መሆኑን ለማረጋጥ ያግዛል። ሥራ ዕድል ተፈጥሮለታል የተባለው የከተማዋ ነዋሪ የት ተቋም ላይ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረለት፣ ስንት ብር እንደሚከፈለው የሚያሳዩ መረጃዎች በአግባቡ እንዲደራጁ ሶፍትዌሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ቋሚ የሥራ ዕድል ስለመፍጠሩ ባለበት ሆኖ መረጃውን ወደ ሥራና ክህሎት ቢሮ ማድረስ ያስችለዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የቢሮው አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን አሃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህንን አፈጻጸም በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራትም ከእስካሁኑ በተሻለ ደረጃ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ልዩ ዕቅድ በማዘጋጀት ከጥቅምት 1 ቀን እስከ ሕዳር መጨረሻ ድረስ የሚቆይ ሰፊ የንቅናቄ ተግባር ተፈፃሚ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ይህ በመደረጉ የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላሉ ተብለው በተለዩ ባለድርሻ አካላት (በግንባታ፣ በከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት በመሳሰሉት) ብቻ በተለዩ ጸጋዎች ላይ በመጪው ሕዳር ወር ለ20 ሺህ 900 ተደራጅተው እየተጠባበቁ ላሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

 ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በከተማዋ ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ የሚከተለው ከአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ያገኘነው መረጃም በመዲናዋ ከ2010 እስከ 2017 በጀት ዓመት ድረስ የተፈጠረውን ቋሚ የሥራ ዕድል ያመላክታል፡፡ በመረጃው መሰረት፡-  በ2010 በጀት ዓመት ለ101 ሺህ 787፣ በ2011  በጀት ዓመት ለ103 ሺህ 243፣ በ2012 በጀት ዓመት ለ213 ሺህ 287፣ በ2013 በጀት ዓመት ለ262 ሺህ 701፣ በ2014 በጀት ዓመት ለ397 ሺህ 380፣ በ2015 ለ377 ሺህ  887፣ በ2016  በጀት  ዓመት ለ291 ሺህ 577  ዜጎች እንዲሁም  2017 በጀት  ዓመት ለ366  ሺህ 44  ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ለሥራ ዕድል መፈጠር የተለዩ ፀጋዎችን ፈቅዶ ተጠቃሚ ከመሆን ጋር በተያያዘ የአመለካከት ጉድለት ወይም ሥራን የማማረጥ ሁኔታ በስፋት የሚታይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰብሃዲን፤ ይህንን ለመቅረፍ ከከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም  ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በትብብር የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከወጣቶቹ ወላጆች ጋርም እንዲሁ የግንዛቤ ፈጠራ መድረኮችን በማዘጋጀት ሥራን ያከበረ፣ ሠርቶ በመለወጥ የሚያምን፣ ዕምነቱንም በተግባር የሚገልጥ፣ በሥራው ውጤት ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡

አያይዘውም፤ የፈጠራ ሃሳብ ላላቸው ዜጎች ራሱን በቻለ ስትራቴጂ ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚደረግላቸው ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ በማስቻል፤ ድጋፍ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል። የከተማዋ ነዋሪ ሥራ አጥ ወጣቶች በከተማዋ ባሉ 119 ወረዳዎች አስፈላጊውን መረጃ በማሟላት መመዝገብ፣ መሰልጠንና በከተማዋ ባሉ የሥራ ዕድል አማራጮች ላይ መሰማራት ስለሚችሉ ይህን ዕድል መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review