ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ እንደራሴዎች

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ እንደራሴዎች
  • Post category:ፖለቲካ

መንግስት ግጭቶችን ለመፍታት ሰላማዊ መፍትሔን ያስቀድማል

መጪውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማከናወን መንግስት በቂ አቅም አለው

ያለፈው 2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ልማቶችንና ስራዎችን ያከናወነችበት ነው፡፡ “ይቻላሉ” ተብሎ የማይታሰቡ ጉዳዮች እውን የሆኑበት ዓመት ነው፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች እና የፌሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብስባ ላይ ያደረጉት ንግግር ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የመንግስትን ገቢና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የማዕድንና የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት፣ የአረንጓዴ አሻራን ግብን በማሳካትና በሌሎችም መስኮች በተከናወኑ ስራዎች ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

የ2018 ዓ.ም መባቻ የዘመናት የቁጭት ምክንያት እና የትብብርና አንድነት ማሳያ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የተመረቀበት፣ በወርሃ መስከረም መጀመሪያ ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ መውጣት የጀመረበት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች መሰረት የተጣለበት በኢትዮጵያ ታሪክ የሚወሳ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት እንደሆነ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

ፕሬዝዳንቱ መንግስት በ2018 በጀት ዓመት ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት፣ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን እና የፍትህ ስርዓቱን በማዘመን በትኩረት እንደሚሰራ መጠቆማቸው አይዘነጋም። የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታውን በማፋጠን፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን በመደገፍ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እንዲሁም በሌሎች መስኮችም በርካታ ስራዎችን በማከናወን በጥቅሉ በኢኮኖሚ ረገድም የ9 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡  

ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች የጋራ ስብሰባ ባቀረቡት የመንግስት የ2018 በጀት ዓመት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በመንተራስ የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሰላምና ፀጥታ

የምክር ቤት አባላት መንግስት ግጭቶችን ለመፍታት ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት የሚሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው በሌላ በኩል አሁንም የሰላምን ጥሪ ባለመቀበል ህዝብን ለስቃይ እየዳረጉ ያሉ ሀይሎችን ለማስቆም ምን እየተሰራ ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽም፤ ኢትዮጵያ ደካማ ሆና እንድትኖርና በሁለት እግሯ መቆም እንዳትችል የሚሰሩ ሀገራት አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ጥቅምን በሚጎዳ መልኩ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት ከእነዚህ አካላት ጋር የሚሰሩ ከሆነ የተሟላ ሰላም ማምጣት እንደሚያስቸግር ጠቁመዋል፡፡

“በአፍሪካ በመሳሪያ አፈሙዝ በማሸነፍ ስልጣን የያዙ ሀይሎች ቢኖሩም አንዳቸውም ለሀገራቸው ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ አልቻሉም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያም ኢህአዴግ በሀይል አሸንፎ ስልጣን ቢይዝም ለሰላሳ ዓመታት ሰላም የነበረበትን አካባቢ እንኳን ሳይቀር ከስንዴ እርዳታ ማውጣት አልቻለም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ ጥያቄ ካላቸው ሀይሎች ጋር ውይይትን በማስቀደም ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ሸኔ ጋር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ከፊሉ ሀይል ወደ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል፡፡ በትግራይም ካሉ ወገኖች ጋር በመወያየት ሰላም እንዲፈጠር በማድረግ ከፊሎቹ ስልጣን ተሰጥቷቸው እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከምንም በፊት ከግል ይልቅ የሀገር ጉዳይን በማስቀደም እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በኦሮሚያም ሆነ አማራ ክልል የሰላምን ጥያቄ ባለመቀበል እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀይሎች “ተላላኪና ዓላማ የሌላቸው ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “መንግስት አሁንም ጥያቄ አለን ከሚሉ ሀይሎች ጋር ለመወያየት በሩ ክፍት ነው፡፡ ማንም ሰው ሰላማዊ መንገድን መርጦ፣ ህግና ስርዓት አክብሮ የሚመጣ ከሆነ ለመታረቅ ብቻ ሳይሆን አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡

ያደሩና አሁን መፈታት የማይችሉ ችግሮችን ደግሞ አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር በማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። ከውይይትና ምክክር ባሻገር የቆዩ በደሎችንና ቁስሎችን በሽግግር ፍትህ አማካኝነት በእርቅና ፍትህ ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። የታጠቁ ሀይሎችን ደግሞ ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ ለማቋቋምና ወደ ሰላማዊ ህይወት ለማስገባት ሀብት ተመድቦ እየተሰራበት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከታጠቁ ሀይሎች መካከል ለመደራደር ለመንግስት ጥያቄ የሚያቀርቡና የሚነጋገሩ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ የሚኖሩ፣ አዲስ አበባ ጭምር የሚገኙና መንግስት “እንዲታረቅ” የሚጠይቁ ሀይሎች ሳይቀሩ “እንዳትደራደሩ” በሚል እንደሚያደናቅፉና ይህም አሳዛኝ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ “አሁንም ለሰላማዊ ትግል በራችን ክፍት ነው፤ ካልተደመርንና ካልተጋገዝን በስተቀር የኢትዮጵያን ችግር ባጠረ ጊዜ መፍታት አይቻልም” ሲሉ የሀገርን ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት መተባበር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በፌዴራል መንግስትና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ወደጎን በማድረግ የህወሓት ቡድን ከውጭ ሀይሎች ጋር በመሆን ዳግም ጦርነት ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ የትግራይን ክልል ሰላማዊ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው? የሚል ጥያቄም ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽም፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት ሕወሓት ያካሄደው ህገ ወጥ ምርጫ እንዲሰረዝ፣ ምርጫውን መሰረት በማድረግ የተቋቋመው ህጋዊ ያልሆነው መንግስት እንዲፈርስና ምክር ቤቱ እንዲበተን፣ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም፣ የታጠቁ ሀይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የፀጥታና መከላከያ ጉዳዮችን የሚመለከተው የፌዴራል መንግስትን ብቻ እንደሆነ መግባባት መደረሱን አብራርተዋል፡፡

በአማራና ትግራይ ክልሎች “የይገባኛል ጥያቄ” የሚቀርብባቸው አከራካሪ አካባቢዎችን በተመለከተም በህገ መንግስቱ መሰረት በህዝብ ወሳኔ ምላሽ እንደሚያገኝ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የህወሓት ቡድን በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቀያቸው እንዳይመለሱ በማድረግ እየፈጠረው ያለው ቀውስ ህዝብ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው።

የወልቃይት ጉዳይ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ካልተፈታ ዘላቂ የሆነ ሰላምን ማምጣት እንደማያስችል ተናግረዋል፡፡

ሕወሓት በሰከነ መንገድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አክብሮ በመንቀሳቀስና ትክክለኛ ጉባኤ በማድረግ ህጋዊ ፓርቲ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከውጊያ ይልቅ የትግራይ እናቶች የሚፈልጉትን ሰላም ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የፌዴራል መንግስቱ ዝግጁ እንደሆነና በትግራይ በኩል ያሉትም ይህንን በመገንዘብ መስራት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤት የሀገራዊ ምክክሩ ሂደቱን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል የምክክሩ አጀንዳዎች ተሰባስበዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮቻችን ለመፍታት መፍትሔ ይሆናል ያሉ አካላትም በሂደቱ ተሳትፈዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ “አያስፈልግም” ያሉት ደግሞ አልተሳተፉም፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ በርካታ ጠቃሚ ግብአቶች የተገኙበትና ቀሪ ተግባራትም ሂደቱን ጠብቆ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

ከመጪው 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘም ያሉ የፀጥታ ሁኔታዎችን በማንሳት ምርጫ ላይደረግ ይችላል በሚል የሚነሱ ስጋቶችን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል። ለዚህም መንግስት በቂ አቅም አለው። አማራጭ ድምፆች ያሉበት ምክር ቤት እንዲኖር መንግስት ከባለፈው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተሻለ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር በኃላፊነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ሪፎርም

ሌላው ከምክር ቤት አባላት የተነሳው ጥያቄ መንግስት መልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ ምን እየሰራ ይገኛል? የሚል ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም፤ የህግ አስከባሪ ተቋማት ላይ ሪፎርም በማድረግ የተሻለ ቁመና እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚታየውን የህዝብን እሮሮ ለመቀነስም የተለያዩ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚሰጡበት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተጀምሯል፡፡ አሁን ላይም 18 የመሶብ አንድ ማዕከላት ተቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ የሚጨመሩ ሶስት ማዕከላትን በመጨመር በዚህ ዓመት 100 ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በፊፎርሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተሰራው ስራም ውጤት መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ወጣቶች በአምስት ሚሊዮን የኮደርስ ንቅናቄ ስልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቅት አግኝተዋል። ይህም ለብዙ ስራዎች አጋዥ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

ማህበራዊ ጉዳይ

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ምን እየተሰራ ይገኛል? የሚልም ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዋናው ቅድመ ልጅነት ላይ መስራት ስለሆነ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ለመምህራን ስልጠና በመስጠት፣ በቨርቸዋል በማስደገፍ ትምህርትና ፈተና በመስጠት፣ መጽሐፍትን ተደራሽ በማድረግ፣ በትምህርት ለትውልድ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል፣ አዋኪ ተግባራትን በመከላከልና በተማሪዎች ምገባ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ጤናን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት 63 ሚሊዮን ዜጎች በጤና መድህን ታቅፈዋል፡፡ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ከመስራት ባሻገር 60 ቢሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ እየቀረቡ ይገኛሉ። የካንሰር ህክምና ወጪ 60 በመቶ በመንግስት እየተሸፈነ ነው፡፡ የውጭ ባለሀብቶች መጥተው እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ሲሆን አሁንም የጤና መሰረተ ልማቶችን በማልማት ረገድ ሰፊ ስራዎች እንደሚጠበቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች

ከምክር ቤት አባላት በኢኮኖሚ ዘርፍ የሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማነት ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ከአንድ ዘርፍ ይልቅ ብዝሃ ዘርፍና ብዝሃ ተዋናይ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል የሚል እምነት ተይዞ የተነደፈው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው በእጅጉ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመንግስትና የህዝብ አጋርነት በርካታ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ለዚህ ማሳያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማንሳት የሚቻል ሲሆን ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ 48 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ችላለች፡፡ እያንዳንዱ ችግኝ ከጅምሩ አንስቶ እስከሚተከልበት ድረስ ባለው ሂደት አንድ ዶላር ያዋጣል ተብሎ ቢታሰብ 48 ቢሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል አውጥታለች ማለት ነው፡፡ ይህንን ማሳካት የተቻለውም ከ25 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚው አንደኛው ስብራት የገቢ አሰባሰብን ማሳደግ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሪፎርሙም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡ ሀገራዊ ለወጡ የመጣ አካባቢ መንግስት የሚሰበስበው ገቢ 170 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በተያዘው ዓመት አንድ ትሪሊዮን ብር እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓላማ የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ ሲሆን፤ በ2016 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ከወጪ ንግድ የተገኘውን ገቢ በተያዘው ዓመት በአራት ወራት ብቻ ማሳካት እንደተቻለና ይህም ውጤት እየመጣ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

የውጭ ዕዳንም በተመለከተ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እዳ እንዳለባት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአፍሪካ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ግን ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ እዳ ያለባቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የወሰደችው ብድር በአጭር ጊዜ ብዙ መክፈል የሚጠይቅ የብድር ስርዓት ነው። ይህ ዕዳ እንዲሸጋሸግ ከአበዳሪዎች ጋር ድርድር በማድረግ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከ4 እስከ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በረጅም ጊዜ እንዲከፈል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ “ኢትዮጵያ አሁን ዕዳ ለመክፈል ችግር የለባትም፡፡” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችትም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻፀር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ከአስር እጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የቢዝነስ ከባቢን (Ease of Doing Bussiness) ለማሻሻል በተወሰዱ እርምጃዎችም ለረጅም ጊዜ ቆሞ የነበረው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የማድረግ ጥረት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የኢኮኖሚ እድገቱን በተመለከተም በየዘርፉ ብንመለከት ግብርና ባለፈው ዓመት 7 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡ ለማሳያነትም በ2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ሩዝ ታመርት ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት 63 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል። የስንዴ ምርትን ብንመለከት በሀገራዊ ለውጡ ማግስት 47 ሚሊዮን ኩንታል ይመረት የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከ280 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ በለውጡ ማግስት ይመረት ከነበረው ቡና የሚገኘውን ገቢም ባለፉት ዓመታት በተሰራው ስራ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት 13 በመቶ ሲሆን በተለይ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግና ሀይል ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት የኢትዮጵያ ሪፎርም ስኬታማ፣ ለብዙ ሀገሮችም ምሳሌ የሚሆንና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተወደሰ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድም በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ገቢ የተገኘበት ዓመት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ አገልግሎትን በመሸጥ (Export of Service) 8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ከሚልኩት ወይም ከሪሚታንስ 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ደግሞ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል፡፡ “የኢትዮጵያ እድገት ጥሩ አፍንጫ ያለው ሰው በ‘ሽታ’ ያውቀዋል፤ ጥሩ ዓይን ያለው ሰው ያየዋል፤ ጥሩ ጆሮ ያለው ሰው በመስማት ይረዳዋል፤ ለመላ አፍሪካ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡” ሲሉ ነው የገለፁት፡፡

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን ለማቃለል ምን እየተሰራ ነው? የሚለው ሌላኛው ከምክር ቤት አባላት የተነሳ ጥያቄ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ የዋጋ ግሽበት ከባለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ያለፈው ዓመት ረግቦ የታየበት ነው። ይህም የሆነበት የምርት አቅርቦትን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን በማጠናከር፣ ድጎማ (440 ቢሊዮን ብር ለሴፍቲኔት፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ ደመወዝና የተለያዩ ነገሮች) በማድረግ በተሰራው ስራ ነው፡፡ ይህ የድጎማ ወጪ ሀገራዊ ለውጡ ሲመጣ ከነበረው ዓመታዊ የኢትዮጵያ በጀት የሚበልጥ ነው፡፡ የጥቅምት ወር የዋጋ ግሽበትም 11 ነጥብ 7 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ ይህም አመርቂ ውጤት ነው፡፡ በተያዘው ዓመት ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ርብርብ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡

የጋዝ ምርትን በተመለከተም በሶማሌ ክልል ጋዝ ማምረት በተጀመረበት አካባቢ ብቻ 21 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ፊት መጠን ያለው የጋዝ ክምችት እንዳላት ተረጋግጧል፡፡ የድፍድፍ ነዳጅ ክምችትም እንዲሁ ከፍተኛ እንደሆነ መረጋገጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታም ልክ በቅርቡ እንደተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የጋዝ ምርት በተጨማሪ በ24 ወራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ አንድ ሺህ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሀይልና ሌሎች ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣው ለነዳጅና ማዳበሪያ ግዢ ነው፡፡ ሁለቱን በሀገር ውስጥ መተካት ከተቻለ ለልማት የሚሆን ከፍተኛ ሀብት ማዳን እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

በዳንጎቴ ኩባንያ የሚለማው የማዳበሪያ ፋብሪካ በዓመት 30 ሚሊዮን ኩንታል የዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ምዕራፍ ሁለት የጋዝ ፋብሪካ፣ አንድ ሺህ ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት፣ የነዳጅ ማጣሪያና መሰል መሰረተ ልማቶች ግንባታ 10 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ተናግረዋል፡፡

የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክትም በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለውና በአስር ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባ ነው፡፡ ሲጠናቀቅም በአፍሪካ ትልቁ የአየር ማረፊያ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ሌላው ከምክር ቤት አባላት የቤት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ምን እየተሰራ እንደሆነ የተነሳ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የቤት ባለቤት ማድረግ ስለማይቻል ቢያንስ በአቅሙ ተከራይቶ መኖር የሚችልበትን አማራጭ ለመፍጠር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ከማጠናቀቅ አኳያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት መንገድን ብቻ ብናነሳ በፌዴራል መንግስት የሚገነቡ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁ 346 የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። በሀይል ማመንጨትና የመብራት ማስተላለፊያ ስራዎች በርካታ ቢሊዮን ብር የሚጠይቁ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙና ከስራው ስፋት አኳያ ያሉ ክፍተቶችን በማረም እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት በ2032 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢያንስ ከአፍሪካ ሁለተኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ ይሆናል፡፡ በ2036 ዓ.ም ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን ይይዛል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review