በስህተት አካዉንቱ ላይ የገባዉን ግማሽ ሚሊየን ብር የመለሰው ጋዜጠኛ

You are currently viewing በስህተት አካዉንቱ ላይ የገባዉን ግማሽ ሚሊየን ብር የመለሰው ጋዜጠኛ

AMN ጥቅምት 22/2018

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነችዉ ባለታሪካችን ሳዲያ ደጀኔ መርካቶ በሚገኝ የንግድ ሱቅ ውስጥ ተቀጣሪ ስትሆን፣ ለተለያዩ ግብይቶች ሂሳብ መክፈል ገቢንም መቆጣጠር ዋነኛ የስራ ድርሻዋ ነው።

ስራዋ ከገንዘብ ጋር በቀጥታ የተገናኘ በመሆኑ በዕለት ከዕለት የስራ እንቅስቃሴዋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ታደርጋለች።

ይሁን እንጂ በህይወቷ ዉስጥ ይህንን ያህል መጠን ያለዉ ገንዘብ ለአደጋ ይጋለጥብኛል ብላ አስባም ተጠራጥራም አታዉቅም።

የቀን ጉዳይ ሆኖ ሰሞኑን የገጠማት ክስተት በህይወቷ ዉስጥ ለከፍተኛ ጭንቀትና ዉጥረት ዳረጓት እንደነበር ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ ተናግራለች።

ሳዲያ ደጀኔ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም 495 ሺህ ብር በዲጂታል ግብይት በስህተት በሌላ ሰዉ አካዉንት ታስገባለች። ብሩ በስህተት የተላለፈዉ ደግሞ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ AMN ጋዜጠኛ በሆነዉ በፍቃዱ መኮንን አካዉንት ነበር።

ለጋዜጠኛ ፍቃዱ መኮንን ግማሽ ሚሊየን ብሩን በስህተት ያስገባችበትን አጋጣሚ ስታስታውሰዉ፣ ስህተቱ ከመፈጠሩ ቀደም ብሎ በሱቃቸው ላደረገው ግብይት በዲጂታል አማራጭ ክፍያ መለዋወጣቸውን ትናገራለች።

በዛው ቅፅበት ለሌላ ደንበኛ 495 ሺህ ብር ዝውውር በማድረግ የዕለት ስራዋን የቀጠለችው ሳዲያ፣ አመሻሽ ላይ በስም መመሳሰል ወደ ጋዜጠኛው ማስገባቷን ትረዳለች።

በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆና ወዲያው ወደ ባንክ ቤት ሄዳ ጉዳዩን ለማስረዳት ብትሞክርም ሰዓቱ ምቹ አለመሆኑን ትረዳለች።

ሁኔታው እሷንና ቤተሰቧን ጨምሮ ለከፋ ጭንቀትና ሀሳብ በመዳረጉ ለሊቱን ሙሉ ያለ እንቅልፍ ማሳለፋቸውን ትናገራለች።

ገንዘቡ በስህተት የተላለፈለት ጋዜጠኛ ፍቃዱም ይህንን ያህል መጠን ያለዉ ገንዘብ ከማያዉቀዉ ሰዉ ያለምንም ምክንያት በአካዉንቱ ገቢ በመደረጉ ከፍተኛ ድንጋጤ እንደተፈጠረበት ይናገራል።

ጉዳዩን ለባለቤቱ ብቻ እንዳስረዳትና ” የሰዉ ሃቅ በአካዉንቴ ገቢ ተደርጓል” በሚል ጭንቀት ምሽቱን እንዳሳለፈ ያስረዳል።

ሌሊቱ እንደ አመት ነበር የረዘመባት ሳዲያ በበኩሏ በጠዋት በመነሳት አካውንቱ ወደሚገኝበት የባንክ ቅርንጫፍ ስታመራ የቀደማት አልነበረም።

ለባንኩ ባለሙያዎች በስህተት ግማሽ ሚሊየን ብር ማስተላለፏን ታብራራለች።

የባንክ ባለሙያዎችም ወደ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ስልክ በመደወል የተፈጠረዉን ስህተት ያስረዱታል።

ጋዜጠኛዉ ፍቃዱም ባንኩ ስልክ ሲደዉልልለትና ጉዳዩን ሲያስረዳዉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማዉ ተናግሯል።

ዕለታዊ ስራውን አከናውኖ እንደጨረሰ ወደ አካዉንቱ የገባዉን ገንዘብ ለመመለስ ወደ ባንኩ ሊመጣ ማቀዱን ያበስራቸዋል።

ጋዜጠኛው በሰዓቱ በባንኩ በመገኘት በስም ስህተት የገባለትን ገንዘብ በታማኝነት ይመልሳል።

ምንም ወሮታ ሳይፈልግ ገንዘቡን በፍጥነት መመለሱ ከልክ በላይ ደስታን የፈጠረባት ባለታሪካችን፣ ዳግም የተወለድኩበት ቀኔ ብቻም ሳይሆን በዘመኔ እንደዚህ አይነት ታማኝ ሠው መኖሩንም እንዳምን ረድቶኛል ብላለች።

በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እየሰራ የሚገኘው ጋዜጠኛ ፍቃዱ መኮንን በበኩሉ፣ አስተዳደጌን ጨምሮ ሙያዬ የሠውን ነገር ከመፈለግ ይልቅ ታማኝ መሆንና ህዝብን ማገልገል ትልቅ ዋጋ እንዳለው አስተምሮኛል፣ለዚህም ነው ገንዘቡን የመለስኩት በማለት ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል አብራርቷል።

ለራስም ሆነ ለሀገር ብሎም ለተሰማራንበት ሙያ ታማኝ መሆን ፍሬው ጣፋጭ ከመሆኑም በላይ በፈጣሪም ዘንድ የተወደደ መልካም ስራ በመሆኑ፣ ሁሌም ታማኝነትን የህይወታችን መርህ ልናደርግ ይገባል ብሏል።

በሚካኤል ሂሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review