55ኛው የኒው ዮርክ ማራቶን ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የሰጠው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች በርካታ የአትሌቲክሱ የአሁን እና ነባር ከዋክብቶች ይሳተፉበታል።
በወንዶች የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና አትሌት ኤሉድ ኪፕቺጌ ተሳትፎ የአትሌቲክስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአትሌቲክሱ የተፎካከሩት ሁለቱ አትሌቶች ዛሬም በኒው ዮርክ ጎዳናዎች ላይ ይሮጣሉ።
የ43 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀለ በአትሌቲክሱ ለ26 ዓመታት የዘለቀ ታሪክ አለው።ቀነኒሳ በዓለም መድረክ በመሮጫ መም ላይ ካሳለፋቸው ስኬታማ ዓመታት በኋላ እ.አ.አ 2014 ፊቱን ወደ ማራቶን አዙሯል።
በወቅቱ በፓሪስ ማራቶን 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ4 ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት በመጀመሪያ ውድድሩ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል። እ.አ.አ በ2019 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ በማሸነፍ እና የግል ምርጥ ሰዓቱን በማስመዝገብ ድርብ ድል አስመዝግቧል።
አትሌቱ ለንደን እና ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል።
ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ኦሊምፒክ በተመለሰበት የእ.አ.አ 2024 33ኛ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን ተሳትፎ 39ኛ ቢወጣም በ42 ዓመቱ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ ታሪክ የተወዳደረ በእድሜ ትልቁ አትሌት በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርቷል።
የ40 ዓመቱ ኬንያዊው አትሌት ኤሉድ ኪፕቾጌ ለ26 ዓመታት የዘለቀ የአትሌቲክስ ቆይታ ያለው ሲሆን ከመሮጫ ትራክ ውድድር ይልቅ የማራቶን ስኬቱ ጎልቶ ይነሳል።
ኪፕቾጌ እ.አ.አ በ2013 በሃምቡርግ ማራቶን የመጀመሪያ ውድድሩን በማራቶን አድርጎ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ በመግባት አሸንፏል።እ.አ.አ. በ2022 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ አንደኛ በመግባት የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ጨብጧል።
እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ እና እ.አ.አ በ2020 በቶሊዮ በተደረጉ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያዎች በማራቶን አግኝቷል።
በኦስትሪያ ቪዬና እ.አ.አ በ2019 በተደረገ ማራቶን 1 ሰዓት ከ59 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ በመሮጥ ከሁለት ሰዓት በታች ማራቶንን የሮጠ የመጀመሪያው አትሌት ቢሆንም የዓለም አትሌቲክስ መስፈርቶችን ያላሟላ ውድድር በመሆኑ ውጤቱ ሳይጸድቅ ቀርቷል።
ሁለቱ አትሌቶች ከእድሜያቸው መግፋት አንጻር የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት ባይወስዱም በውድድሩ ላይ መሳተፋቸው ትልቅ ድምቀትን የሚፈጥር እና ተቀናቃኝነታቸውን ዳግም የሚቀሰቀስ ነው።
ደሬሳ ገለታ በኒው ዮርክ ማራቶን የሚሳተፍ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው።
የወቅቱ የኒው ዮርክ ማራቶን አሸናፊ በትውልድ ሶማሊያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነው አብዲ ናጌዬ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን የወርቅ ባለቤቱ ታንዛንያዊው አልፎንስ ሲምቡ፣ ኬንያውያኑ ቤንሰን ኪፕሩቶ እና አሌክሳንዳር ሙቲሶ በወንዶች ውድድር ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በሴቶች አትሌት ጎይቲቶም ገብረስላሴ ትሳተፋለች።
በትውልድ ኢትዮጵያ በዜግነት ኔዘርላንፋዊ የሆነችው ሲፋን ሀሰን፣ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ኬንያዊቷ ሼሊያ ቼፕኪሩይ፣ ሌላኛዋ ኬንያዊ ሄለን ኦቢሪ እና አሜሪካዊቷ ሳራ ሆል ከሴቶች የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች በተመሳሳይ የ100 ሺህ የአሜሪን ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በተጨማሪም የቦታውን ክብረ ወሰን ለሚሰብር አትሌት ተጨማሪ 50 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይበረከታል።
አጠቃላይ ለተሳታፊ አትሌቶች 900 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገደማ ሽልማት መዘጋጀቱን የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል።
የኒው ዮርክ ማራቶን እ.አ.አ በ1970 የተጀመረ ውድድር መሆኑን መረጃዎችን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።