3ኛውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ የትግራይ ክልል ያዘጋጃል
በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት ለተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየዉ 3ኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በአይነትም በብዛትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ ቀጄላ መንግስት ስፖርት መልክ እንዲይዝ እንደሚከታተልና እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።
የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ለዓለም ኦሎምፒክ መድረክ ተተኪ ስፖርተኞች ከማፍራትም ባሻገር ወጣቶች ከተለያየ ቦታ ወደ አንድ በማምጣት ብዝሃ ባህልን እንዲለዋወጡ አስችሏቸዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር ) በበኩላቸው ሀገርን የሚወክሉ ልዩ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች በእውነተኛ እድሜ ላይ ያሉ ወጣቶችን ስናበቃ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው ወጣቶች ኦሎምፒክ ከአንደኛው የተሻለ ቢሆንም አሁንም በእድሜ በኩል ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።
የሜዳሊያና የዋንጫ ፍላጎት ከዓላማችን ውጭ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ከተደረገው ቁጥጥርና ክትትል ውጭ የሾለኩ ስፖርተኞች እንደአሸናፊነት ሊቆጠሩ እንደማይችሉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን ስፖርት ሊያሳድገው የሚችለው እውነተኛ ውድድርና ስልጠና መሆኑን ያከሉት ፕሬዚዳንቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ከዚህ በኋላ በየዓመቱ እንደሚካሄድ ዶ/ር አሸብር አብስረዋል።
3ኛውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ትግራይ ክልል ለማስተናገድ እድሉን መዉሰዱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል