በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ እና ውጤታማ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
ውይይቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና በትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አዘጋጅነት ”የጋራ መግባባት ለሰላማዊ መማር ማስተማር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የመንግስት ትምህርት በቤቶች በትምህርት ልማት ዙሪያ አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገቡ ይገኛሉ፣ለዚህም የመምህራን እና ርዕሳነ መምህራን ሚና ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ትምህርት ቤቶች ከሀይማኖት እና ፖለቲካ የነጹ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ አንዳንድ አካላት ግን የተለያዩ አጀንዳዎችን በማንሳት ትምህርት ቤቶችን የሁከት እና ብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሚሞከረው ድርጊት ተቀባይነት አይኖረውም ሲሉ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶች የሰላም እና እውቀት መገኛ መሆን አለባቸው ለዚህም መመምህራን እና ርዕሰ መመህራን ኃላፊነት ላቅ ያለ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አፆንዖት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ከማል ለሰላማዊ ለውጤታማ መማር ማስተማር የትምህርት ማህበረሰብ ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
መድረኩ በተለይም ትምህርት ቤቶች የእውቀት መገቢያ ብቻ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ተማሪዎች እና
ከ70 ሺ በላይ መምህራን እንደሚገኙ ከአዲስ አበባ ትምህርት አስተዳደር ትምሀርት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በሀብታሙ ሙለታ