በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊ ተግባር የሚወገዝና መቼም በማንም ሊደገም የማይገባ ጥቁር ጠባሳ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊ ተግባር የሚወገዝና መቼም በማንም ሊደገም የማይገባ ጥቁር ጠባሳ መሆኑ ተገለጸ

AMN ጥቅምት 24/ 2018 ዓ.ም

በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ጠቅላይ መምሪያና በሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ዝክረ ሰሜን ዕዝ ታስቦ ውሏል፡፡

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ፋይናንስ ስራ አመራር መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል መርጋ ቀልቤሳ ፣ ህዋሃት በራሱ ዜጋ እና አገር ጠባቂ ሰራዊት ላይ በየትኛዉም የዓለም ጫፍ ተደርጎ የማያዉቅ ግፍ የፈፀመ ብቸኛዉ ነዉ በማለት ተናግረዋል።

የሰሜን ዕዝ ለትግራይ ህዝብ ከኪሱ ገንዘብ በማዋጣት የመሰረተ ልማቶችን ከመስራት ጀምሮ ከዕለት ጉርስ ቀንሶ የሚያጎርስ ሰራዊት የነበረ ቢሆንም በህወሃት የስልጣን ጥም እና የሴራ ፖለቲካ ምክንያት በሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ታሪክ የማይረሳው ግፍ መፈፀሙን ተናግረዋል።

በተያያዘ የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል የሰራዊት አባላት የሰሜን ዕዝ መታሰቢያ ቀንን አስበዋል “እንዳይደገም መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል የሰሜን ዕዝ 5ኛ አመት የሰማዕታት መታሰበያ ቀንን በጠቅላይ መምሪያው ስታፍ አባላትና በክፍለጦር አባላት በጋራ በውይይትና በጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት ተዘክሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አካሉ ካሳ በሰሜን ዕዝ በሰራዊታችን ላይ የተፈፀመው ግፍ የማይጠፋ ጠባሳ አሳርፎ ያለፈ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ክፍል በተሰማራንበት የግዳጅ ቀጠና የሀገራችን ሰላም የሚያውኩ ሽብርተኛና ፅንፈኛ ሀይሎችን ከስር መሰረታቸው በማጥፋት ሀገራችን የያዘችውን የልማት ጉዞ በማስቀጠል ህዝብና መንግስት የሰጡንን ሃላፊነት መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የሜካናይዝድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አምስተኛ የሰሜን ዕዝ ሰማዕታት ቀንን ዘክረዋል።

በዕለቱ የተገኙት የማሰልጠኛ ማዕከሉ አዛዥ ኮሎኔል አየለ ወልደ ጊዮርጊስ ባስተላለፉት መልዕክት በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊ ተግባር የሚወገዝና መቼም በማንም ሊደገም የማይገባ ጥቁር ጠባሳ መሆኑን አውስተው የሰማዕታቱን አደራ የምንወጣው ሀገራችን ኢትዮጵያ እያነሳች ያለችውን የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ ከዳር ለማድረስ በሚሰጡን ግዳጆች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ነው ማለታቸዉን የሃገር መከላከያ ሰራዊት ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review