የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሶሪያን ፕሬዝዳንት በኋይት ሀውስ ተቀብለው ሊያስተናግዱ ነው።
አሶሼትድ ፕረስ ከትራምፕ አስተዳደር አገኘሁት ባለው መረጃ፣ የሶሪያው ፕሬዝዳንት አሕመድ አልሻራ ከሳምንት በኋላ በነጩ ቤተ መንግስት ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ ብሏል።
አልሻራ ለ50 ዓመት የዘለቀውን የአሳድ ቤተሰብ አስተዳደር ገርስሰው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባሳለፍነው ግንቦት በሳዑዲ አረቢያ ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በአንድ ወቅት የ10 ሚሊየን ዶላር ማደኛ ወጥቶባቸው የነበሩት የአሁኑ የሶሪያ ፕሬዝዳንት አልሻራ፣ ከ11 ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ሀገራቸውን ለማረጋገት በጥረት ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ ከምዕራቡ ዓለም ጋር እያደሱት በሚገኘው ዲፕሎማሲ፣ በደማስቆ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች እንዲነሱ እና እገዳ የተጣለባቸውን ሀብቶች ወደ ሀገር ቤት ለመመለስም እየሞከሩ ነው።
አሕመድ አልሻራ የቀድሞ የሶሪያ ፕሬዝዳንት ሃፊዝ አሳድ ከቢል ክሊንተን ጋር ከተገናኙ ከ25 ዓመት በኋላ ከአሜሪካ መሪ ጋር የሚገናኙ የመጀመሪያው መሪ ሲሆኑ፣ ኋይት ሀውስን በመጎብኘት ደግሞ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው።
በዋሽንግተን በሚኖራቸው ቆይታም ሶሪያን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ በአዲስ መልክ እየተደራጀ የሚገኘውን አይኤስ በጋራ ለመዋጋት ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዳዊት በሪሁን