የኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት የኢንቨስትመንት ፎረም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ተከፍቷል።
ፎረሙ ከሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣የኩባንያ መሪዎች እና ባለሀብቶችን በጋራ በማሰባሰብ አዳዲስ የኢኮኖሚ ትብብር መስኮችን በመፈተሽ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት ያለውን የኢኮኖሚ አጋርነትን ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ ነው።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የMEDEF International ምክትል ፕሬዝዳንት ፋብሪስ ለ ሳሼ፣የፈረንሳይ የውጭ ንግድ እና የኢኮኖሚ ምቹነት ሚኒስትር ተወካይ ኒኮላ ፎሂሴ እና የአውሮፓ ኮሚሽን የአፍሪካ ጉዳዮች ተወካይ ዳይሬክተር ጌዛ ስትራመር ንግግር አድርገዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ እና እያመጣ ያለውን ውጤት እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንደፈጠረ ሰፊ ያለ ገለጻ አድርገዋል።
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያቀረቡ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው የኢኮኖሚ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለውን ጉዞም አድንቀዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ተቋማት እና በአውሮፓ ኢንተርፕራይዞች መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር እንደ ዋና መሠረት የሚያገለግል መሆኑን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡