ኢትዮጵያ በቢሾፍቱ ለማስገንባት ያቀደችው አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያን የንግድ እና ኢኮኖሚ ማዕከል በማድረጉ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተነግሯል።
ይህ የተባለው በዛሬው ዕለት በፈረንሳይ ፓሪስ መካሄድ በጀመረው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ የገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሽዴ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የኤርፖርቱ ግንባታ አጋር የሆነው ዓለም አቀፉ አማካሪ ድርጅት ዳር አል-ሃንዳሳህ እና የግንባታው ከፍተኛ አማካሪ ዓለም አቀፍ ተቋም ኬፒኤምጂ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው በአፍሪካ ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገትና ቀጠናዊ ውህደትን በማስፋፋት ዋና ማዕከል የማድረግ አቅም እንዳለው በዚሁ ወቅት ተነስቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ይህ አዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አውሮፕላን ማረፊያ ለዕድገት፣ ለብልፅግናና ለዓለም አቀፍ ትስስር መግቢያ በር ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን በመጥቀስ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታውን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
የኤርባስ የአፍሪካ ኃላፊ የሆኑት ፌዴሪኮ ቡልውቶ በበኩላቸው የቢሾፍቱ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እንደ ኤምሬትስ እና ኳታር ኤርዌይስ ካሉ ግንባር ቀደም የአየር መንገዶች ጋር ተወዳዳሪ እና ዓለም አቀፍ አስተሳሳሪ የመሆን አቅም እንደሚያጎናጽፈው መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁሟል።