ከሌላ ሰው የተከራየውን ተሽከርካሪ ለወንጀል ፈጻሚዎች ያከራየን ግለሰብ በቁጥጥ ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ግለሰቡ በአንድ አዳር ከወንጀለኞቹ 6ሺ ብር እንደሚቀበል ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው 30 ሜትር ፍየል ቤት አካባቢ በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ የሞባይል ስልክ ቅሚያ ወንጀል እንደሚፈፀም የሰሚት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ መረጃ ይደርሰዋል፡፡
ፖሊስ ጣቢያው ባሰባሰበው መረጃ ብሩክ ተሾመ የተባለው ግለሰብ ተሽከርካሪ በመከራየት ቀን ቀን የግል ትራንስፖርት ወይም በተለምዶ ራይድ ሲሰራ እንደሚውልና ማታ ማታ መኪናውን ለወንጀለኞች እንደሚያከራይ ፖሊስ መረጃ ይደርሰዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ግለሰቡን እና ቅሚያ የሚፈፅሙትን ወንጀል ፈፃሚዎች ለመያዝ በተደረገው ክትትል በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ሰባራ ባቡር አካባቢ ተጠርጣሪው መኪናውን ሲያሽከረክር በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት የተለያዩ 10(አስር) ሞባይል ስልኮችን በተሽከርካሪው ውስጥ እንደተገኘና መኪናውን ቀን ሲሰራበት ውሎ ማታማታ ለወንጀል ፈፃሚዎች በአንድ አዳር በ6ሺ ብር እንደሚያከራይ በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
የቀሩትን ሌሎቹን ወንጀል ፈፃሚዎች በቁጥጥርስ ስር ለማዋል ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡