በአገልግሎት አሰጣጥ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት በመነጋገርና በመፍታት ረገድ የእንጠያየቅ መድረክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የንግድ ጽ/ቤት በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በገበያ መረጋጋት እና በመሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ዙሪያ ተገልጋዩን ሕዝብ እና የስራ ሃላፊዎችን ፊት ለፊት ያገናኘ “የእንጠያየቅ” መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ እና የክፍለ ከተማው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሸማች መብት ጥበቃ ኮሚቴ አባላት እና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዱ ከበደ የከተማ አስተዳደሩ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ ዋጋን በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን እየተከናወነ እንደሚገኝ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል።
በዚህም ዘመናዊ የግብርና ምርቶች መሸጫና ማከፋፈያ ማዕከላትን ገንብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ አስችሏል፤ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ቦታዎችን የማስፋትና አቅማቸውን የማሳደግ ተግባር በማከናወኑ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንደተቻለ አቶ ዘውዱ ከበደ ተናግረዋል።
በከተማዋ የዋጋ ንረትን ማስተካከል ያስቻለ ተግባራት ቢከናወኑም እንኳን፤ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም ይህን መሰል የእንጠያየቅ መድረክ መካሄዱ ፋይዳው የጐላ ነው ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፍ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችም በከተማዋ የዋጋ ንረትን ለማስተካከል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አድንቀው ቢስተካከሉና ቢታረሙ ብለው ያሰቧቸውን ጥያቄዎችን አንስተው ከመድረኩ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በታምሩ ደምሴ