የአርሰናል ደጋፊ የሆኑት አዲሱ የኒውዮርክ ሲቲ ተመራጭ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ

You are currently viewing የአርሰናል ደጋፊ የሆኑት አዲሱ የኒውዮርክ ሲቲ ተመራጭ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ

AMN-ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም

የኒውዮርክ ሲቲ አዲሱ ተመራጭ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ የዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ ርእስ ሆነዋል።

የ34 ዓመቱ ወጣት ፖለቲከኛ ለእግርኳስም ባላቸው ፍቅር መነጋገሪያ መሆን ችለዋል።

በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ዩጋንዳ የተወለዱት ማምዳኒ ገና በሰባት ዓመታቸው ነበር ከቤተሰባቸው ጋር የኒውዮርክን ምድር የረገጡት።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆኑት ዞህራን ማምዳኒ በፖለቲካ እሳቤያቸው እጅጉን ግራ ዘመም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ለድሆች በሚያሳዩት ርህራሄ ደጋፊዎች በርክቶላቸዋል። ለእግርኳስ ያላቸው ውዴታ ደግሞ ወጣቱን ስቦላቸዋል።

በከንቲባነት ካስመረጣቸው ጉዳይ አንዱም ይህ ነው። በርከት ያለውን ወጣት እና የገንዘብ አቅም የሌላቸው እገዛ አድርገውላቸዋል።

ዞህራን ማምዳኒ እግርኳስን እንዲወዱ ያደረጋቸው አጎታቸው እንደሆኑ ይናገራሉ።

በአፍሪካ እንደመወለዳቸው በርከት ላሉ የአህጉሪቱ ተወላጆች እድል ይሰጥ ለነበረው የአርሰን ቬንገር አርሰናል ቦታ እንዲኖራቸው አድርጓል።

በተለይ በልጅነት እድሜያቸው ያዩት ምንም ሽንፈት ሳይገጥመው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያሸነፈው የ2004 ቡድንን አብዝተው ይወዱታል።

የፖሊቲካውን ምህዳር ሙሉ ለሙሉ ከተቀላቀሉ በኋላ ጊዜ ቢያጥራቸውም የአርሰናል ጨዋታ አያመልጣቸውም።

በመኪናቸው ውስጥ ጭምር ከሹፌራቸው ጀርባ ሆነው በስልክ የአርሰናልን ጨዋታ እንደሚመለከቱ የአትሌቲክ ፅሁፍ ያሳያል።

የአርሰናል የቅርብ ተፎካካሪ የሆኑ ቡድኖችን ጭምር ጊዜ ሲያገኙ ይከታተላሉ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ማንችስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን ሲረታ “ፈጣሪ ይባርክህ ሩበን አሞሪም” ብለው እንደነበር አትሌቲክ በፅሁፉ አስፍሯል።

ለክሪኪት ስፖርትም ትልቅ ቦታ ያላቸው ማምዳኒ ከአርሰናል ተጫዋቾች ለቡካዮ ሳካ እና ዊሊያም ሳሊባ የተለየ ውዴታ አላቸው።

በአጠቃላይ በእግርኳሱ ያለው ፖለቲካ መስመር የሳተነው የሚሉት ማምዳኒ ፊፋ ይህን እንዲያስተካክል ይሞግታሉ።

አሁን አሁን ደጋፊዎች እንደ ሸቀጥ እየታዩ ነው የሚሉት ፖለቲከኛው በተለይ የትኬት ዋጋ መጨመር እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትም በዝግጅቱ ሀገራቸው ጭምር የምትሳተፍበት የ2026 የዓለም ዋንጫ ውድድር ፊፋ የተመነው የትኬት ዋጋ እንዲያስተካክል ጥሪ አቅርበው ነበር።

ጥር 2026 የኒውዮርክ ከንቲባነት ስራቸውን የሚጀምሩት ማምዳኒ በተለይ የአካባቢው ሰዎች በቅናሽ እንዲስተናገዱ ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ዞህራን ማምዳኒ የኒውዮርክ ከንቲባ ሆነው እንዲመረጡ ትልቅ እገዛ ያደረገላቸውን እግርኳስ በተለይ በአስተዳደራዊ ጉዳይ ለውጥ እንዲያመጣ እሰራለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review