በወጥ ብቃት እየተጓዘ የሚገኘው አርሰናል በ11ኛ ሳምንት የሊግ መርሃግብሩ ሰንደርላንድን ይገጥማል።
ከስምንት አመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ሰንደርላንድ አስደናቂ ጉዞ ላይ ይገኛል።
በሜዳው ስታዲየም ኦፍ ላይት እስካሁን ሽንፈት ያልገጠመው ክለቡ ዛሬ ምሽት 2:30 የሊጉ መሪን ያስተናግዳል።
በሰንደርላንድ ትልቅ ልዩነት ፈጣሪ የሆነው ግራኒት ዣካ የቀድሞ ክለቡን የሚገጥምበት አጋጣሚምም ይፈጠራል።
ስዊዘርላንዳዊው አማካይ ወደ ባየር ሊቨርኩሰን ከማቅናቱ በፊት በሰሜን ለንደኑ ክለብ ሰባት አመታትን ማሳለፉ ይታወሳል።
የ33 ዓመቱ አማካይ ለመድፈኞቹ 225 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አከናውኗል። ከእነዚህ ውስጥ 113ቱን ያደረገው በአሁኑ የክለቡ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ እየተመራ ነበር።
አርሰናል መሸነፍ ቀርቶ ግብ የማይቆጠርበት ክለብ ሆኗል።
በሁሉም ውድድር ካደረጓቸው ስምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች በአንዱም ግብ አልተቆጠረበትም። ከእነዚህ ውስጥ አራቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ናቸው።
አርሰናል አምስተኛ የሊግ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ካሸነፈ ከ48 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።
በዛሬው ጨዋታ በአርሰናል በኩል ቪክቶር ዮኬሬሽ በጉዳት ምክንያት አይሳተፍም።
ሚካኤል አርቴታ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር አድሮጎ ያስጀመረው እና ሁለት ግቦችን ከመረብ ማሳርፍ የቻለው ሚካኤል ሜሪኖን ሊያሰልፍ ይችላል።
ሰንደርላንድ በውድድር ዓመቱ ምንም እንኳን በሜዳው ሽንፈት አይግጠመው እንጂ ከአርሰናል ጋር ያለው ክብረወሰን ደካማ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በመጨረሻ ካደረጉት 15 የሊግ ጨዋታ አርሰናል 10 አሸንፎ በአምስቱ አቻ ተለያይቷል።
በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ የቪቶ ፔሬራ ተተኪ ያላገኘው ወልቭስን ይገጥማል። ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኤቨርተን ከፉልሃም ፣ ዌስትሃም ዩናይትድ ከ በርንሌይ የሚጫወቱ ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ