ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድን

You are currently viewing ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድን

 . ሲከታተሉ የቆዩ ከ8 ሺህ 800 በላይ የመጨረሻ ዙር ተሳታፊ ወጣቶች ነገ ልምምዳቸውን ያጠናቅቃሉ
• በዓለም ባንክ የጋራ ትብብር ሲፈፀም የቆየውን መርሃ ግብር ተሞክሮ በመውሰድ በራስ አቅም ተፈፃሚ ለማድረግ ታቅዷል

የሠው ልጅ ከህፃንነት እስከ እርጅና ባለው የሕይወት ጉዞ ውስጥ ሲቆይ፤ በሁሉም ምዕራፍ የራሱን ልዩ ለዛ ያገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የወጣትነት ዕድሜ ክልልን የመሰለ ልዩ ተፈጥሯዊ ጸጋ የሚላበስበትን ዘመን የመሰለ የለም፡፡ በወጣትነት ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ፣ ለአገር እና ከዚያም ለሚሻገር በጎ ውጤት የሚሆን ዕምቅ አቅም ይገኛል፡፡ ዕውቀትና ክህሎት ይያዛል፡፡ ለዚህም ነው “ወጣት የነብር ጣት” የሚል አገርኛ አባባል የተነገረው፡፡

በዚህ ፅሑፍም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር ስለቆየው “የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር” ዳስሰናል፡፡ በተለይ ነገ (ማለትም ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም.) በይፋ የሚጠናቀቀውን የመርሃ ግብሩን ሂደትና አፈፃፀም እንፈትሻለን፡፡ የሥራ ላይ ልምምዱ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶችን፣ ዕድሉን የፈጠሩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ሚና እንዳስሳለን፡፡

ወጣት ዮሀንስ ጌትነት፤ ነዋሪነቱ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ነው። ትምህርቱን እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትሏል። በ2016 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ ፈተና ወስዶ ውጤት ስላልመጣለት በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገድዶ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ብቁ ሙያተኛ ሆኗል። ለዚህም የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ተሳታፊ መሆኑ ጠቅሞታል፡፡

ለሦስት ወራት ያለትምህርት እና ያለ ሥራ የቆየው ወጣት ዮሀንስ፣ በእነዚህ ጊዜያት ድብርት ውስጥ እስከመግባት ደርሶ እንደነበር በማስታወስ፣ ያንን ጊዜ እና አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዲህ ሲል በንፅፅር ያስረዳል፤ “በሦስቱ ወራት ውስጥ ሥራ ለመፈለግ ተንቀሳቅሼ ነበር። አሰሪዎች የሚጠይቁት አንድ ነገር ‘ምን ሙያ አለህ?’ የሚል ነው፡፡ ሥራ ለማግኘት ጉልበት እና ፍላጎት ብቻውን ትርጉም እንደሌለው ተገነዘብኩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ስለ ሥራ ላይ ልምምድ መረጃ ጎረቤቶቼ ሰጡኝ፡፡ በመረጃው መሰረት የሚጠየቁትን መስፈርቶች በማሟላት ተመዘገብኩ፡፡ በእንጨት ሥራ በተሰማራ ድርጅት ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ ማድረግ ከጀመርኩ በኋላ፣ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ የሥራ ፍቅሬ ጨምሯል፡፡ ገቢ ማግኘት ችያለሁ፡፡”

ወጣት አብርሃም ተስፋዬ እንደ ወጣት ዮሀንስ ሁሉ፤ ከሦስት ዓመት በላይ ያለ ትምህርት እና ሥራ ያሳለፈው ጊዜ ያስቆጨዋል፡፡ እነዚህን ግዜያትም፤ “ትምህርትም ሥራም ስለሌለኝ በጣም የሚያስጨንቅ ጊዜ ነበር ሳሳልፍ የነበርኩት፡፡ በዚህም ሙሉ ትኩረቴን በኦንላይን የሚተላለፉ የቨርቹዋል ጌሞች ላይ አደረግሁ፡፡ በሂደት እኔን መሰል ወጣቶች እንገናኝ ጀመር፡፡ በአቻ ግፊት ተፅዕኖ ወደ ሱስ የምገባበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በጣም መጥፎ መስመር ውስጥ እየገባሁ ነበር” በማለት ያስታውሳል፡፡

የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ነዋሪው ወጣት አብርሃም፣ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር አማካኝነት፣ በግርማ፣ ሕይወትና ጓደኞቻቸው የእንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ ድርጅት ያገኘው ሙያዊ ክህሎት፣ ልምድና ውጤት ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን ያነሳል፡፡ ይህንንም፤ “ለሦስት ዓመታት ያክል ያሳለፍኳቸውን አስቸጋሪ ልምዶች፤ ለ6 ወራት የቆየሁበት የሥራ ላይ ልምምድ አክሞልኛል፡፡ በ6 ወራት ውስጥ ትኩረቴ ሁሉ ሥራ ብቻ ሆኗል። አዳዲስ ሙያዎችን ለመልመድ ያለኝ ፍላጎና ጉጉት ጨምሯል። ከድርጅቱ ባለቤት እና ከሥራ ባልደረቦቼ የማገኛቸው ልምዶች እኔን በጥሩ መልኩ ገንብተውኛል፡፡ የሥራ ግንዛቤዬ ተለውጧል፡፡ በሥራዬ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ ገቢ ማግኘት፣ ካገኘሁትም ላይ መቆጠብ ጀምሬያለሁ፡፡ ከሰፈሬ አልፌ ወደ ሌሎች ከተሞች በመሄድ በሙያዬ ሠርቼ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ጀምሬያለሁ፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ የተሻለ ሕይወት እንደምኖር አምኛለሁ፡፡ ቤተሰቤ በእኔ መለወጥ ደስተኛ ሆኗል፡፡” ሲል አብራርቷል፡፡

አቶ ግርማ አለኸኝ ይባላሉ፡፡ የግርማ፣ ሕይወትና ጓደኞቻቸው የእንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅታቸው በ2013 ዓ.ም. በመቋቋም እየሠራ ይገኛል። ምርት ከማምረት ጎን ለጎን ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡ የሥራ ላይ ልምምድ የሚያደርጉ ወጣቶችንም በመቀበል መሰረታዊ ሙያ እያስጨበጠ ይገኛል፡፡  ወጣት ዮሀንስ ጌትነት እና አብርሃም ተስፋዬን ጨምሮ ስምንት ወጣቶችን በመቀበል በድርጅቱ ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ እያደረጉ ይገኛሉ።  ከዚህ በፊት በነበረው መርሃ ግብር 14 ወጣቶችን ተቀብለው  የሥራ ላይ ስልጠና መስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡

“የሥራ ላይ ተለማማጆች ወደ ድርጅታችን የሚመጡት ሙያውን ለማወቅና በሙያው ሠርተው ለመለወጥ ፍላጎት ካላቸው ብቻ ነው፡፡ አሁን ላይ ስልጠናቸውን እያጠናቀቁ ያሉት ስምንቱ ወጣቶች ይህንን ሙሉ በሙሉ ያሟሉ ናቸው፡፡ ይህም ባሳለፍናቸው ስድስት ወራት ማረጋገጥ ተችሏል” የሚሉት አቶ ግርማ፣ ከወጣቶቹ ጋር ያሳለፏቸውን ስድስት ወራት እንደሚከተለው በአጭሩ ይተርካሉ፤ “ወጣቶቹን እንዳገኘኋቸው፤ ስለ ፍላጎታቸው ጠይቄ ተረዳሁ፡፡ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ከእኔም ጋር እንዲቀራረቡ በነፃነት አወያየኋቸው፡፡ ከዚያም ድርጅቱን በአካል አዩ፤ ወደ ሥራ ላይ ልምምድ ገቡ፡፡ የሥራ ላይ ልምምዱ  እንዴት መቁረጥ፣ ማሸግ፣ መገጣጠም … እንደሚችሉ መሰረታዊ ሙያውን በወረቀት ላይ አሳየኋቸው፡፡ ያሳየኋቸውን ስለመረዳታቸው የቤት ሥራ በመስጠትና በማረም ሙያው ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡ አደረግሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ከማሽኖች፣ ከሙያው፣ ከሥራው ጋር በሚገባ ተዋወቁ፡፡ አሁን ላይ እኔ ባልኖር እንኳን፤ ሥራዎችን ጥንቅቅ አድርገው የሚሠሩ ብቁ ሙያተኞች ሆነዋል፡፡”

ምክትል ሥራ አስኪያጁ አክለው እንዳስረዱት፤ የሥራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩት ወጣቶች የሥራ ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ ሥነ ምግባራቸው ተሻሽሏል፡፡ የሥራ ሰዓትን ያከብራሉ፤ የተሰጣቸውን ሥራ በአግባቡ ይፈፅማሉ፡፡ ቢቀሩ እንኳን አስፈቅደው ነው፡፡ በሳይት ላይ በመውጣት ከነባር ሠራተኞች ያልተናነሰ ሥራ እስከ መሥራት ደርሰዋል፡፡ በሁለት ወር ውስጥ ከ30 ቤት በላይ የኪችን ካቢኔት ገጥመዋል፡፡ ይህ አፈፃፀማቸው ልምድ አለን ከሚሉት ባለሙያዎች በእጥፍ ብልጫ አለው። በዚህ ሥራቸው እያንዳንዳቸው እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ ገቢ አግኝተዋል፡፡ በሥራ ያገኙትን ገቢ በመቆጠብ ማሽን እስከመግዛት የደረሱም አሉ፡፡

ዘናጭ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተሰጠ ባለው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ላይ እየተሳተፉ ካሉ የግል ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ በ2009 የተቋቋመው ይህ ድርጅት የስፖርት ትጥቆችን ያመርታል፤ ለነጋዴዎች ያከፋፍላል፡፡ ከ280 በላይ ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ድርጅቱ፤ በመጨረሻው ዙር የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር እንዲሳተፉ ከተመለመሉ ወጣቶች መካከል ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት 100፣ ከወረዳ ሦስት ደግሞ 15 በድምሩ 115 ወጣቶችን እንደተቀበለ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ትግስት ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡

ወደ ዘናጭ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለሥራ ላይ ልምምድ ከገቡት ወጣቶች መካከል፤ የስድስት ወር ስልጠናቸውን አብዛኞቹ ማጠናቀቃቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጇ፤ የተወሰኑት በተለያየ ምክንያት ማቋረጣቸውን አልሸሸጉም፡፡ በሥራ ላይ ልምምዱ በተገቢው ሁኔታ የተሳተፉ እና ያጠናቀቁ ወጣቶች ያገኟቸውን ጥቅሞች በተመለከተም፤ “የሥራ ላይ ልምምዱን የመጀመሪያ አንድ ወር እንዳጠናቀቁ፤ ለአምስት ወራት ያክል ድርጅቱ በየወሩ 1 ሺህ 500 እንዲሁም ተጨማሪ በየሳምንቱ 300 ብር እየከፈላቸው አቆይቷቸዋል።  እነዚህ ወጣቶች ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው፣ የሥራ ፍቅርና ተነሳሽነታቸው ጥሩ የሆነ፣ ከነባር የድርጅቱ ሠራተኞች እኩል ምርታማ መሆን የቻሉ ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉት በሙሉ በአሁኑ ወቅት ከድርጅቱ ጋር በቋሚ ሠራተኛነት ለመቀጠል ውል በመፈራረም ላይ እንገኛለን” በማለት ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ መርያ ሀሰን እና ወጣት ስብሀት ግርማ ዘናጭ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሥራ ልምምድ እያደረጉ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ናቸው፡፡ ባነጋገርናቸው ጊዜ እንዳስረዱት ከሆነ፤ የሥራ ላይ ልምምዱ በሥራ አጥነት ያሳለፏቸውን አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያት በማስረሳት ራስን በመቻል እና ለታላቅ ስኬት በመዘጋጀት ሃሳብ ውስጥ እንዲገኙ እንዳስቻላቸው አልሸሸጉም፡፡

ከ10ኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ እና ትዳር መስርታ ትኖር እንደነበር የገለጸችው ወይዘሮ መርያ ሀሰን፣ ይህንን ዕድል በማግኘቷ ተጠቃሚ እንደሆነች፤ “የሥራ ላይ ልምምድ ከመጀመሬ በፊት ሕጻን ልጄን በመንከባከብና በማሳደግ በቤት ውስጥ ባሉ ስራዎች ብቻ አተኩር ነበር፡፡ ወደዚህ ድርጅት ከገባሁ በኋላ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ጋር በተያያዘ መሰረታዊ ሙያዎችን አግኝቻለሁ። ከነባር ሠራተኞች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ ብቃትን ይዣለሁ፡፡ በዚህም በድርጅቱ በቋሚ ሠራተኛነት ለመቀጠር ችያለሁ፡፡ ለእኔና ለቤተሰቤ የሚሆን ገቢ ፈጥሬያለሁ፡፡ በቀጣይ የተሻለ ደረጃ መድረስ እንደምችል ተስፋ ሰንቄያለሁ” በማለት ታስረዳለች፡፡

“ትምህርቴን ከ10ኛ ክፍል በማቆም፤ ያለ ሥራ ተቀምጬ ነበር፡፡ ይህ መሆኑ ብዙ ጫና ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ከቤተሰብ ጋር እስከመጋጨት ደርሼም አውቃለሁ። የሥራ ላይ ልምምድ ከጀመርኩ በኋላ በራስ መተማመኔ አድጓል፡፡ ከሰው ጥገኛነት ወጥቻለሁ፡፡ ለቤተሰቦቼ ዳቦ ገዝቼ መግባት ችያለሁ፡፡ ወደፊት ከራሴ አልፌ ከጓደኞቼ ጋር በመደራጀት ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ድርጅት ለማቋቋም አልማለው፡፡ ለእኛ የተመቻቸው ዕድል ለሌሎችም ወጣቶች መመቻቸት አለበት” የሚለውን ሃሳብ ያጋራን ደግሞ ወጣት ስብሀት ግርማ ነው።

ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ዓመት፣ የትምህርት ደረጃቸው 12ኛ እና ከዚያ በታች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጥነው ወደ ሥራ የሚገቡበትን ዕድልን ማመቸት ዓላማ አድርጎ ሲተገበር የቆየ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን፤ በመርሃ ግብሩ ከሚሳተፉት ወጣቶች መካከል 60 ከመቶው ድርሻ የሴቶች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የሥራ ላይ ልምምድ እንዲደረግባቸው የሚመረጡ ድርጅቶች የተቀመጠላቸውን መስፈርት ያሟሉ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች፡- ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው፣ ቢያንስ 6 ቋሚ ሠራተኞችን የቀጠሩ፣ 4 የሥራ ላይ ተለማማጆችን የሚቀበሉ መሆን አለባቸው፡፡ የተሰማሩባቸው ዘርፎችም፡- ማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎት፣ የከተማ ግብርና መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የሥራ ከባቢ ምቹ ማድረግ አለባቸው፡፡     

እንደ አቶ ሰብሃዲን ገለጻ፤ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዓለም ባንክ ትብብር የሚከናወን ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. የተጀመረው መርሃ ግብሩ በአምስት ዓመቱ ውስጥ 49 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በማቀድ የተገገበረ ሲሆን፤ የአምስት ዓመታት ቆይታውን ነገ (ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም.) ያጠናቅቃል፡፡ ነገ በሚጠናቀቀው የመጨረሻው ምዕራፍ የሥራ ላይ ልምምድ ላይ 15 ሺህ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 9 ሺህ 615ቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወጣቶች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ከውጭ አገር የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡

ከ9 ሺህ 615ቱ የመጨረሻ ዙር የሥራ ላይ ልምምድ ተሳታፊ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣቶች መካከል 8 ሺህ 884 ያህሉ ልምምዳቸውን አጠናቀው ነገ ይመረቃሉ ሲሉም አክለዋል፡፡

በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር የሚሳተፉ ወጣቶች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች በተመለከተ አቶ ሰብሀዲን በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ ወጣቶች ወደ ሥራ ላይ ልምምድ ከመግባታቸው አስቀድሞ ፍላጎታቸው ይጠየቃል፣ የድርጅቶች/ተቋማት የሥራ ባህል ይነገራቸዋል፡፡ በዚህ ላይ በግልፅ በመወያየት አሠሪ ድርጅቶች እና የሥራ ላይ ተለማማጅ ወጣቶች እንዲወስኑ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ወደ ሥራ ላይ ልምምዱ ይገባሉ፡፡ የስድስት ወር የሥራ ላይ ልምምዳቸውን እንደጨረሱ የቆዩባቸው ድርጅቶች የስድስት ወራት የሥራ ልምድ ይጽፉላቸዋል፡፡ የምስክር ወረቀትም ይሰጣቸዋል፡፡ በቆይታቸው ለትራንስፖርት ወጪ የሚሆን በቀን 133 ብር ወይም በወር 2 ሺህ 926 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ልጅ ያላቸው ወጣት ሴቶች በተለየ ሁኔታ ለልጆቻቸው እንክብካቤ የሚሆን ተጨማሪ 945 ብር በየወሩ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለሦስት ወራት ለሥራ ማፈላለጊያ የሚሆን የትራንስፖርት ወጪ በቀን 133 ብር ታስቦ ይከፈላቸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለው እንዳብራሩት፤ ወጣቶቹ ከሙያዊ ስልጠና በተጨማሪ ለ12 ቀናት የሚቆይ የሕይወት ክህሎት ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ በየሦስት ወሩ ደግሞ መሰረታዊ የኮምፒውዩተር ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ በየወሩ የአቻ ለአቻ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ስለ ተቋማት የሥራ ባህል፣ ስለ ሥራ ላይ ችግርና መፍትሄ የመሳሰሉትን እንዲገነዘቡ ይደረጋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ሙያዊ ክህሎት ያላቸው፣ የሥራ ልምድ ያካበቱ፣ ዕውቅና ካላቸው ድርጅቶች የሥራ ልምድ የተሰጣቸው ዜጎችን ደግሞ ገበያው ይፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ካለፉ ወጣቶች አብዛኞቹ ቋሚ የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ የራሳቸውን ሥራ በግልና በቡድን በመሥራት ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ በቅጥር እየሠሩ ያሉት ወጣቶች ከ5 ሺህ እስከ 34 ሺህ ብር ድረስ ወርሃዊ ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡

በአምስት ዓመቱ የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ጥቅል ውጤት በጥናት ለማረጋገጥ በገለልተኛ አካል ለማስጠናት ዕቅድ መያዙን የጠቆሙት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን፤ ይህም ሆኖ አብዛኛው የሥራ ላይ ልምምድ ያደረገ ወጣት ሥራ ላይ መሆኑን በሥራና ክህሎት ቢሮ መዋቅር የተሰበሰበ መረጃ እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል፡፡

በመንግስት እና በዓለም ባንክ የጋራ ትብብር ሲፈፀም የቆየውን ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ተሞክሮ በመውሰድ በራስ አቅም ተፈፃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አቶ ሰብሀዲን ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ መርሃ ግብሩ ሕዳር አጋማሽ 2018 ዓ.ም. በይፋ ይጀመራል፡፡ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመረጡ 20 ወረዳዎች ላይ ለሚጀመረው መርሃ ግብር እንደ ከተማ አስተዳደር 145 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፤ 3 ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ወጣቶቹ የሥራ ላይ ልምምዳቸውን የሚያደርጉባቸው 1 ሺህ 100 ድርጅቶችም ተለይተዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review