ወይዘሮ ዙቤዳ ሃይረዲን የተክለ ሃይማኖት አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ያገኛቸው በልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጤና ፅህፈት ቤት በተክለሃይማኖት ጤና ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሊያሳድሱ መጥተው ነው፡፡ ከአገልግሎቱ ጋር ያላቸውን ቁርኝት፣ “ክፍያው 80 ብር በነበረበት ጊዜ ጀምሮ ተጠቃሚ ነኝ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆን መቻላቸው እንዳስደሰታቸውም አክለዋል፡፡
ወይዘሮ ዙቤዳ በአስተያየታቸው፣ “የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በተለይ እንደ እኔ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ብዙ ጊዜ የህመም ስሜት ሲሰማኝ ቶሎ ብዬ ደብተሬን ይዤ ወደ ጤና ጣቢያ እሄዳለሁ፡፡ በምርመራው መሰረትም የሚታዘዝልኝን መድሃኒት በመውሰድ ጤናዬን እጠብቃለሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የህመም ስሜት ባይሰማኝም ጤናዬ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ምርመራ አደርጋለሁ፡፡” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
“የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸው የስኳር ህመም ታካሚ ባለቤቴን ከሞት ታድጎልኛል፡፡ በየጊዜው መድሃኒት ይወስዳል፡፡ ለዚህም የሚወጣው ወጭ ከአቅማችን ጋር አብሮ ስለማይሄድ ክትትል ላናደርግ እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን የኢኮኖሚ ችግራችን በዚህ ጤና መድህን ተፈትቷል፡፡ አጠቃላይ ቤተሰቡ ጤናችንን ለመጠበቅ አስችሎናል” ሲሉም አክለዋል፡፡
“ጤና መድህን የጤናችን ዋስትና ነው፤ ለህክምና ጨርቅ አንጥፎ ከመለመን የሚገላግል፣ ወገን ለሌለው ወገን የሚሆን እንዲሁም ገመና ሸፋኝ ነው” ሲሉ የእሳቸውም ሆነ የቤተሰባቸው ጤና ተጠብቆ እንዲኖሩ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው በጤና ጣቢያው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ወንድይፍራው ታደሰ ይባላሉ፡፡ “እኔና ቤተሰቦቼ ቅድመ ምርመራም ይሁን ህክምና የምናደርገው በጤና መድህናችን ነው፡፡ ‘ገንዘብ የለኝም እንጂ የጤናዬን ጉዳይ ማወቅ እፈልግ ነበር’ ብለን በሃሳብ ብቻ አንቀርም፡፡ የደም ግፊትም ሆነ የስኳር ምርመራ እናደርጋለን” ሲሉ ነው ጤና መድህኑን በመጠቀም ጤናቸውን እየተከታተሉ እንዳሉ የገለጹልን፡፡
“እግሬን ያመኛል፤ ይህን ለመታከም ስሄድ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የደም መርጋት የመሳሰሉትን ምርመራዎች አደርጋለሁ፤ በዚህም ጤነኛ መሆኔን አረጋግጣለሁ” የሚሉት አቶ ወንድይፍራው፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸው ጤናቸውን ቀድመው ለመጠበቅ እንዳገዛቸው ገልፀዋል፡፡
በጤና ጣቢያው ጠቅላላ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ቤተልሔም ወንድወሰን በበኩላቸው፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን እያንዳንዱ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ በዓመት አንድ ጊዜ በሚከፍለው
ክፍያ ዓመቱን ሙሉ ህክምና የሚያገኝበት እና ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ወደ ህክምና ሲመጡ ምርመራውም ሆነ መድሃኒቱ በነፃ በመሆኑ ማህበረሰቡ ቅድመ ምርመራ የማድረግና ህመሙንም በመከታተል ጤናውን በመጠበቁ ረገድ ትልቅ ለውጥ እንዳለው አክለዋል፡፡
ዶክተር ቤተልሔም አያይዘው፤ በገንዘብ ምክንያት ምርመራ ያለማድረግም ሆነ መድሃኒት የማቋረጥ እንዲሁም ተስፋ የመቁረጥ ችግሮችን በመቅረፍ ጤናው ላይ ትኩረት የሚሰጥ ማህበረሰብ ተፈጥሯል፡፡ ይህንንም በጤና ጣቢያው ቅድመ ምርመራ ከሚያደርጉና ህክምናቸውን ከሚከታተሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መመልከት መቻላቸውን ገልጸው፤ ማንኛውም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መንግስት ባመቻቸለት እድል ተጠቅሞ ጤናውን መጠበቅ እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጤና ፅህፈት ቤት የተክለሃይማኖት ጤና ጣቢያ ሜዲካል ምክትል ዳይሬክተርና በጤና ጣቢያው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ተመሰለው ቸርነት በበኩላቸው፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሲባል ዜጎች ጤናማ በሚሆኑበት ወቅት በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ከመድህን ቋቱ ወጪ በማድረግ የጤና ወጪያቸው የሚሸፈንበት ነው፡፡ ይህም የመደጋገፍ ባህልን ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው፣ በአባላት መካከል የእርስ በርስ መደጋገፍ እንዲፈጠር አድርጓል። የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ በመሆናቸው አኗኗራቸውም ጭምር ለበሽታ የሚያጋልጥ ነው። ይህንን በሽታ ከፍሎ የመታከምና መድሃኒት ገዝቶ የመጠቀም አቅማቸው ስለማይፈቅድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆኑ የሚፈልገውን ምርመራ አድርጎ ጤናው ያለበትን ሁኔታ እንዲያውቁ፣ ከታመሙ ደግሞ የህክምና ክትትል በማድረግ ጤናቸው እንዲመለስ የማድረግን እድል የሚፈጥር ነው፡፡
በተለይ ደግሞ እንደ ስኳር፣ የደም ግፊት የመሳሰሉ ህመሞች ያሉባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ሆነው ህክምና ባያደርጉ ኖሮ ከዓይነ ስውርነት እስከ ድንገተኛ ሞት ይዳረጉ ነበር። ይህ እንዳይሆን በጠዋቱ በሽታው ተለይቶ እንዲታከሙ፣ ጤናቸውን እንዲከታተሉና ህመማቸውም ቶሎ መፍትሄ እንዲያገኝ ያደርጋቸዋል ሲሉ ያለውን የጤና ጠቀሜታ ገልፀዋል፡፡
በተክለሃይማኖት ጤና ጣቢያ አዳዲስና ነባር አባላት እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ተመሰለው ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ወረዳ አምስት 1 ሺህ 655 እና ወረዳ ሰባት 1 ሺህ 291 ነባር የጤና መድህን አባላት እድሳት አድርገዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እና ቤት ለቤት በመዞር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡
አቶ ማሙሽ ደበሬን ያገኘናቸው ሌላኛው ቅኝት ባደረግንበት ማይጨው ጤና ጣቢያ አዲስ የጤና መድህን ለመመዝገብ በመጡበት ወቅት ነው፡፡ “የምኖረው ኑሮና ለህክምና የማወጣው ወጪ ባለመመጣጠኑ የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆንን መርጫለሁ” ይላሉ፡፡

የአቶ ማሙሽን ሃሳብ የሚጋሩት ወይዘሮ ሰላማዊት ጌታቸው የጤና መድህን ተጠቃሚ በመሆናቸው ሲያማቸው ያለስጋት ለመታከም እና ጤናቸውን ለመጠበቅ እንዳገዛቸው ነግረውናል፡፡
በማይጨው ጤና ጣቢያ ከ32 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት እንደሚያገኝ የሚናገሩት ደግሞ የጤና ጣቢያው ምክትል ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ አበበ ሳህሌ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በ2017 ዓ.ም ከ1 ሺህ 800 በላይ አባወራና እማወራ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ሲሆኑ በ2018 ደግሞ 2 ሺህ 500 የሚሆኑ ነባርና አዳዲስ አባላትን ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ነው የነገሩን፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖረው የማህበረሰብ ክፍል የአቅሙን በማዋጣት ዓመቱን ሙሉ የሚታከምበት ስርዓት ነው፡፡ እነዚህ አካላት በማንኛውም ወቅት የጤና እክል ሲገጥማቸው ህክምና የሚያገኙበት እንዲሁም ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉበት በመሆኑ ጤናቸውን በመጠበቁ ረገድ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ይላሉ፡፡ በቤተሰብ ጤና ቡድን ማህበረሰቡ ድረስ በመውረድ በሽታ የመከላከል፣ የማከም እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡
ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በኢ መደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ተሰማርተው የሚኖሩ ዜጎችን የሚያካትትና ማህበረሰቡን ለማገልገል የቆመ አንዱ የጤና መድህን አይነት መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን የነገሩን ደግሞ በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአዲስ አበባ የክላስተር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አይካ ናቸው፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚያገኙት የጤና አገልግሎት ዓይነቶችም የተኝቶ ህክምና፣ የተመላላሽ ህክም፣ ቀዶ ህክምና፣ የላቦራቶሪና ሌሎች በህክምና ባለሙያዎች የታዘዙ ማንኛውንም ምርመራ አገልግሎቶችን ሲሆን፤ ነገር ግን በሌሎች ህጎች ሽፋን የተሰጣቸው አደጋዎች፣ ለረጅም ጊዜ የሚሰጡ የኩላሊት እጥበት ህክምና፣ የዓይን መነፅር መግዛትና ሰው ሰራሽ ጥርስ ማስተካከልና ማናቸውም ሩት ካናል(ድድ ስር የሚቆስል) ህክምናዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን (ማዐጤመ) የማይሸፈኑ የህክምና አገልግሎቶች ናቸው፡፡
ዓመታዊ ክፍያውን ራሳቸው የሚከፍሉ እና በራሳቸው መክፈል የማይችሉ በሶስተኛ ወገን የሚሸፈንላቸው የቀጥታ ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ የቀጥታ ተጠቃሚዎች ያሉበት የኑሮ ደረጃ በቅርብ አካላት እየተተቸ የሚመረጡና በከተማ አስተዳደሩ ክፍያው የሚሸፈንላቸው ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ ለማድረግና ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከጤና ቢሮ፣ ከጤና ተቋማት እንዲሁም መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት ጋር በቅንጅት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በዚህ ጤና መድህን ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ አካላት በየዓመቱ በሚያዋጡት መዋጮ ወይም ክፍያ የጤና እክል ባጋጠማቸው ወቅት ካልታሰበ ከፍተኛ ወጪ የሚጠበቁበት አንዱ ስርዓት ነው። ይህ ሲሆን በቤተሰባቸውም ሆነ በራሳቸው ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ታክሞ ለመዳን እና በሚፈልጉት ወቅት የሚፈልጉትን ምርመራ አድርገው ጤናቸው ያለበትን ሁኔታ እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በሽታው ሳይባባስ ከተደረሰበት ቶሎ ታክሞ ለመዳን እና ጤናን ለመጠበቅ አጋዥ ነው ይላሉ፡፡
ህብረተሰቡ አንድ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር አባላት ወደ ምዝገባ ሲሄዱ መሟላት የሚገባቸውን በሙሉ ሟሟላት እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህም የምዝገባና እድሳት ሂደቱን የተቀላጠፈ በማድረግ የአገልግሎት ፈላጊዎችን ጊዜ ገንዘብና አቅም እንደሚያተርፍ መረዳት ይገባል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ዛሬ ነገ ሳይል የምዝገባ ጊዜው አጭር መሆኑን ተረድቶ የምዝገባ ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት አገልግሎት በሚያገኙበት ወይም በሚቀርባቸው ጤና ጣቢያ እስከ ህዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ነባር አባላት እድሳት እና አዲስ አባላት ምዝገባ በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ