ማርን በከተማ

You are currently viewing ማርን በከተማ

• በየካ ክፍለ ከተማ 221 አካላት በንብ ማነብ ስራ የተሰማሩ ሲሆኑ፣ በተያዘው ወር መጨረሻ 27 ሺህ 525 ኪሎ ግራም ምርት እንደሚሰበሰብ ተገልጿል

ከተሞች የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሞተር ናቸው፤ በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 ያወጣው ጥናታዊ ፅሑፍም ይህንኑ ያመላክታል። ተቋሙ ከተሞች በማህበራዊ፣ በኮኖሚያዊ እና በከባቢያዊ ስርዓቶቻችን ውስጥ ምን ድርሻ አላቸው? (What are Cities and What Role do They Play in our Social, Economic, and Environmental Systems?) በሚል ርዕስ ያስነበበው ጥናታዊ ፅሑፍ እንደሚያትተው ከሆነ ከተሞች የንግድ፣ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል በመሆን ለሀገራት ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያበረክታሉ፡፡ በዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥም የ85 በመቶ ድርሻ አላቸው።

በአብዛኛው ተዝናኖታዊ ቅኝት ያላቸው የስራ እንቅስቃሴዎች እንደሚዘወተርባቸው የሚገመተው ከተሞች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግብርናንም እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ መጠቀም ጀምረዋል። አይግሮው ኒውስ፣ ‘ምግባቸውን የሚያመርቱ ከተሞች’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ፅሑፍ፣ የከተማ ግብርና በውስን ቦታ ላይ ትርጉም ባለው ደረጃ የከተማ ነዋሪዎችን አኗኗር እያሻሻለ እንደሚገኝ አስነብቧል፡፡ እንደ ሲንጋፖር፣ ዲትሮይት፣ አትላንታ፣ ሚያሚ፣ ለንደን፣ ኒው ዮርክ እና ፓሪስ ያሉ ከተሞች በአነስተኛ ቦታዎች ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ የግብርና ስራዎችን በመስራት ነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡ በዶሮ፣ በወተት፣ በዓሣ፣ በአትክልትና በፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድ ቀላል የማይባል ውጤት አግኝተዋል፡፡ ምርቶቹን ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባሻገር አቀነባብረው ለሽያጭ በማዋልም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ፈጥረዋል፡፡

ሲንጋፖር ከተማ 10 በመቶ ያህሉን የምግብ ፍጆታዋን በከተማ ግብርና ለመሸፈን በቅታለች፡፡ ከተማዋ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ከሚያስፈልጋት የግብርና ምርት ውስጥ 30 በመቶውን በራሷ ለመሸፈን በመስራት ላይም ትገኛለች። ለዚህም ‘30 በ30 ጎል’ የተሰኘ መርሃ ግብ ነድፋ እየሰራች ሲሆን፣ በከተማ ግብርና ዙሪያ ፈጠራን ለማበረታታት 60 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም “የከተማ ግብርና እና የምግብ ዋስትና በሲንጋፖር” (Urban Farms And Food Security In Singapore) በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2021 ያወጣው ፅሑፍ ያትታል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥም የከተማ ግብርና ስራ በስፋት የሚተገበር ሆኗል፤ በተለይ በሰብልና በጓሮ አትክልት፣ ንብ በማነብ፣ በዓሳ ምርት፣ በዶሮና እንቁላል እንዲሁም በወተትና በወተት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ በርካቶች ተሰማርተዋል። በከተማዋ የከተማ ግበርና ልምምድ እለት ከእለት እያደገ መጥቶ ነዋሪዎችም በጓሯቸው በበረንዳቸው፣ በቤቶቻቸው ጣርያና ግድግዳ አትክልቶችን በማብቀል ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በመጠቀም የማር ምርት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እንደሀገር ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የከተማ ግብርና በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ መነቃቃትና ለውጥ ማሳየቱ የሚካድ አይደለም።   የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ አንቆርጫ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ንብ በማነብ ስራ የተሰማሩት አቶ መስፍን ሰይፉ አንድ አብነት ናቸው። ቀደም ሲል በባህላዊ ቀፎ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ንብ የማነብ ስራን የጀመሩት ተጠቃሚው በተጠናከረ መንገድ መስራት የጀመሩት ግን ከሦስት ዓመት ወዲህ እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ከ20 በላይ ዘመናዊ ቀፎ ያላቸው አቶ መስፍን በማር ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ንብ ማነብ ገጠር፣ ከተማ፣ ሰፊና ጠባብ ቦታ ሳይባል በየትኛውም ሁኔታና አካባቢ እንደሚቻልና ጠንክሮ ከተሰራ ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ በኢኮኖሚ ረገድም ተጠቃሚ ያደርጋል የሚሉት አቶ መስፍን፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ብቻ ወደ 200 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ከማር ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ከአምናው በተሻለ መልኩ ማር ለመሰብሰብ አቅደዋል፡፡

ንብ የማነብን ስራ ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ከቤተሰባቸው ጋር ሲያከናውኑ እንደነበርና አሁን ላይ ግን በግላቸው ስለዘርፉ ለማወቅና አስፋፍተው ለመስራት ባደረጉት ጥረት ከ20 በላይ ዘመናዊ ቀፎችን አዘጋጅተው ከእርሳቸው በተጨማሪ ለሁለት ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ። በንብ ማነብ የተሻለ የማር ምርት ተጠቃሚ ለመሆን ለንቦቹ በቂ ውሃና ምግብ ከማቅረብ በተጨማሪ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማሟላት ከምንም በላይ ደግሞ የራስ ተነሳሽነትን ይጠይቃልም ብለዋል፡፡

እንደ አቶ መስፍን ገለፃ፣ በተለይ አሁን በምንገኝበት በዚህ ወቅት አበቦች የሚፈኩበት እንደመሆኑ ለስራው አመቺና የተሻለ የማር ምርት የሚገኝበት ነው፡፡ ንቦች አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ ዛፎች አበባዎችን በመቅሰም እራሳቸውን ይመግባሉ። በራሳቸው ከሚመገቡት በተጨማሪ የተለያየ አበባዎችን በመትከል መመገብና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ውጤታማ ያደርጋል፡፡

ቀፎ ብቻ በማስቀመጥ በዓመት የማር ምርት ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻል አቶ መስፍን ገልጸው፣ የንብ መንጋውን ጠብቆ መያዝና አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ በዓመት ጥራትና ብዛት ያለው የማር ምርት ማግኘት ይቻላል ባይ ናቸው። ከሚደረግላቸው እንክብካቤና ጥንቃቄ መካከልም ተባይ እንዳይገባባቸው፣ በሸረሪት ድር እንዳይጎዱ እንዲሁም የተለያየ በሽታ እንዳያጠቃቸው በተቻለ መጠን የቀፎዎችን ንጽህና እና  የአካባቢያቸውን ጽዳት መጠበቅ ዋንኞቹ ናቸው፡፡

ለንብ ማነብ የተለየ ስሜት እና ፍቅር እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ መስፍን፣ በዓመት ሶስት ጊዜ ጥቅምት፣ ታህሳስ እና ግንቦት ላይ የማር ምርት እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ በንብ እርባታ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ገልፀው፣ በአካባቢያቸው ላሉ ለሌሎች ነዋሪዎች ልምዳቸውን በማካፈል ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ ምክንያት መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ያደታ ዋቁማ፣ አካባቢው በደን የተሸፈነ በመሆኑ ለንብ ማነብ ስራ አመቺ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ንብ ማነብ ተፈጥሯዊ አካባቢን እንደሚፈልግ ገልጸው፣ ወረዳው ለዚህ ስራ ተስማሚ አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በወረዳው በተለይም ጂፋራ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የሚኖሩ 40 አርሶ አደሮች ከሌሎች የከተማ ግብርና ስራዎች ጎን ለጎን ንብ በማነብ ዘርፍ መሰማራታቸውን ጠቅሰው፣ በ70 ዘመናዊ ቀፎዎች የንብ ማነብ ስራን እያከናወኑ ያሉት አንድ አርሶ አደር ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል መፍጠራቸው በማር ምርት ረገድ ትልቅ ተስፋ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ከነዚህ በተጨማሪም በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ከ20 መቶ የሚበልጥ ዘመናዊ ቀፎ በመጠቀም ንብ በማነብ የተሰማሩ 15 አባላት ያሏቸው ሶስት ማህበራትና ግለሰቦች መኖራቸውን አውስተው፣ ከእነዚህም ከባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ የማር ምርት እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ጂፋራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የውሃ ዕጥረት ችግር እንደሚያጋጥማቸው ገልፀው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉን የግብዓት እና የሙያ ድጋፍ በመስጠት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም በመግለፅ፡፡

ክፍለ ከተማው ከሌሎች አንፃር ሲታይ ንብ ለማነብ ምቹና የተሻለ መሆኑን ገልጸው፣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በብዛትና በጥራት ማምረት እንዲችሉ፣ ምርታቸውን እንዴት ማሳዳግ እንደሚችሉ፣ አንድ ቀፎ ወስደው ሁለትና ከዚያ በላይ የማድረግ ወይም የማባዛት ስልጠና እንዲሁም በባለሙያ የተደገፈ የቴክኒክ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ  221 አካላት በግልና በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ ስራ የተሰማሩ  ሲሆኑ፣ አሁን ባለው መረጃ እንደ ክፍለ ከተማ 1 ሺህ 101 ቀፎዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል፤  ከእነዚህም 943 ዘመናዊ ቀፎዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ባህላዊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዓመት ከእያንዳንዱ የማር ቀፎ 25 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት ይቻላል፡፡ እንደ የካ ክፍለ ከተማም በተያዘው ወር መጨረሻ አካባቢ 27 ሺህ 525 ኪሎ ግራም ማር ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህም ንብ የማነብ ስራ በትኩረት ከተሰራበት ተጠቃሚ የሚያደርግ የስራ ዘርፍ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review