ልጆች፤ ስለግል ንፅህና አጠባበቅ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ ስለግል ንፅህና አጠባበቅ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

ልጆች የግል ንጽህና አጠባበቅ ምን ማለት እንደሆነ፣ የግል ንጽህናን መጠበቅ ምን ጥቅም እንዳለው ታውቃላችሁ? አዎ እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የግል ንፅህና አጠባበቅ  እጅን መታጠብ፣ ጥርስን መቦረሽ፣ ፀጉርን መንከባከብ፣ ገላን መታጠብ የሚሉትንና ሌሎችንም ያካትታል። ልጆች የግል ንጽህናን መጠበቅ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንዱና ዋነኛው ጤናማ እንድንሆን ያደርገናል። በተለይም በተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ እንዳንያዝ ያደርገናል፡፡ ሌላው የግል ንጽህናን መጠበቅ በራስ የመተማመን ስሜት እንዲኖረን ያደርጋል።

ልጆች ታዲያ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ሁሉ የግል ንጽህናችሁን መጠበቅ እንዳለባችሁ መዘንጋት የለባችሁም፡፡ ዛሬ ትምህርት ቤት ስለምሄድ ንጽህናዬን ልጠብቅ፣ ወይም ትምህርት ቤት ስለማልሄድ ባልጠብቅም ችግር የለም የሚል  አመለካከት ሊኖር አይገባም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በዛሬው ዝግጅታችን ምንጊዜም የግል ንጽህናቸውን የሚጠብቁ ልጆችን ልምድና ተሞክሮ ልናካፍላችሁ ወደድን፡፡ 

ዳናይት ገዛኸኝ እባላለሁ፡፡ እድሜየ 12 ዓመት ነው፡፡ የአለም ማያ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ፡፡ የግል ንፅህና ገላዬንና ጸጉሬን በመታጠብ፣ ጥፍሬን በመቁረጥና ጥርሴን በመቦረሽ እንዲሁም ንጹህ ልብስ በመልበስ እጠብቃለሁ፡፡ ይህንን የማደርገው ትምህርት ቤት ስሄድ ብቻም ሳይሆን በእረፍት ቀናትም ጭምር ነው። ንጹህ ልብስ የምለብሰው  ትምህርት ቤት ስሄድ ብቻም ሳይሆን ከትምህርት ቤት ስመለስም ነው፡፡ የቤት ውስጥ ስራ ከሰራሁ በኋላም ሆነ ከጨዋታ መልስ እጄን በውሃና በሳሙና እታጠባለሁ፡፡ ትምህርት ቤት በማልሄድበት የእረፍት ቀኔ ለምሳሌ እሁድ ጠዋትም ጭምር ጥርሴን እቦርሻለሁ፡፡

ስሜ በጸጋ ተከተል ይባላል፡፡ የምማረው የአለም ማያ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የግል ንጽህናችንን መጠበቅ ስንችል ራሳችንን ከተለያዩ በሽታዎች መከላከል እንችላለን፡፡ በየትኛውም ጊዜና ቦታ በትምህርት ቤትም ይሁን በቤት ውስጥ እጄን በሳሙናና በውሃ የመታጠብ ልምድ አለኝ፡፡ ቤቴም ልሁን ትምህርት ቤት እጄን ሳልታጠብ ምግብ አልበላም። የሰውነቴንና የልብሴን ንጽህናም እጠብቃለሁ፡፡ ከትምህርት ቤት ውጪ ሰፈር በምውልበት ቀን ልክ ትምህርት ቤት ስሄድ ንጹህ ልብስ እንደምለብሰው ሁሉ ለጫወታም ቢሆን ንጹህ ልብስ ለብሼ ነው የምወጣው፡፡ በሳምንት አንድ ጊዜ ጥፍሬንና ጸጉሬን እቆርጣለሁ። ሁልጊዜ ንጹህ መሆን ነው የምፈልገው። በንጽህና ጉድለት አንድ ቀን ታምሜ ከትምህርት ቤት ቀርቼ አውቃለሁ፡፡ ስለሆነም ሁላችሁም ንጽናችሁን መጠበቅ ያለባችሁ ትምህርት ቤት ስትሄዱ ብቻም ሳይሆን በቤታችሁ ውስጥም መሆን አለበት፡፡

ቃለአብ ደርጉ እባላለሁ፡፡ የአለም ማያ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ፡፡ የግል ንጽህናዬን የምጠብቀው በሁሉም ቦታ ነው፡፡ በትምህርት ሰዓትም ይሁን ትምህርት ቤት በማልሄድበት ጊዜ ከመኝታዬ እንደተነሳሁ መጸዳጃ ቤት እገባለሁ፡፡ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጄን እና ፊቴን በውሃና ሳሙና እታጠባለሁ፡፡ ቤትም ይሁን ትምህርት ቤት ሳልታጠብ ተመግቤ አላውቅም፡፡ ከትምህርት ቤት ስመለስም ዩኒፎርሜን አውልቄ ንጹህ የቤት ውስጥ ልብስ እለብሳለሁ፡፡ ማታ ወደ መኝታዬ ስሄድም ንጹህ የሌሊት ልብስ እለብሳለሁ፡፡ ይህንን እውቀት ያገኘሁት በሳይንስ ትምህርት ነው፡፡ እናትና አባቴም ስለግል ንጽህና አጠባበቅ ሁልጊዜ ያስተምሩኛል፡፡

እንግዲህ ልጆች የግል ንጽህናን አለመጠበቅ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች በማጋለጥ ጤናችሁን ሊያሳጣችሁ፣ ከትምህርት ገበታችሁ ሊያስተጓጉል ከመቻሉም በላይ በራስ የመተማመን ብቃትን ስለሚያሳጣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሁልጊዜ የግል ንጽህናን የመጠበቅ ጉዳይ የሁልጊዜ ተግባራችሁ ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡ 

በለይላ መሃመድ

    

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review