43ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በሻምፒዮናው ላይ በአጠቃላይ 1ሺህ 209 አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከሱዳን እና ታንዛንያ በተመሳሳይ አንድ አንድ አትሌቶች ይወዳደራሉ።
በሴቶች በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት፣ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ እና በ2 ኪሎ ሜትር ውድድሩ ይደረጋል።
8 ኪሎ ሜትር ወጣት፣ 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ እና 2 ኪሎ ሜትር በወንዶች ውድድር የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው።
በሁለቱም ጾታዎች የወጣት ውድድሮች ላይ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በሻምፒዮናው ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ የግል እና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ።
ለአትሌቶች የውድድር እድል መፍጠርና በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም በአሜሪካ ፍሎሪዳ ለሚካሄደው 46ኛው የአለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ሀገር ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን መምረጥ የሻምፒዮናው አላማዎች ናቸው።
ሽልማትን ጨምሮ ለውድድሩ አጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡንም ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።