በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለፅ እንደቆየው የሀገራዊ ምክክር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ሂደቱ ራሱን በቻለ ህጋዊ ማዕቀፍ የሚተዳደር ሲሆን የሂደቱ ውጤቶች ህጋዊ ስርዓትን አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ግንዛቤ ያላቸው አካላት ይስተዋላሉ፡፡
በእርግጥ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ከህግ ፍልስፍናዎች እና መሰረታዊ አስተምህሮቶች ጋር የሚገናኙበት መንገድ እንዳለ አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በሌላ አገላለፅ ሀገራዊ ምክክር ከሥነ-ምግባር፣ ከሞራል ብሎም ከማህበረሰባዊ ስርዓቶች ጋር ተመጋጋቢ እንደሆነ በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ ምክክሮች አስረጂዎች ናቸው፡፡
ከዚህ አንፃር ሂደቱ ህግን እና ህጋዊ ስርዓትን አደጋ ላይ ከመጣል ይልቅ በምን መልኩ አዎንታዊ ድጋፍ እንደሚኖረው የተለያዩ መዛግብት አመክንዮአዊ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡ ለአብነት ያህልም የሚከተሉት ሀሳቦች ይህንኑ እንዲያብራሩ ቀርበዋል፡፡
1. የሕግ አስፈፃሚ አካል ማንነት
ሕግ እና ሕጋዊ ስርዓቶች የሕግ አስፈፃሚውን አካል ማንነት በማሳወቅና የስልጣን ገደቡን በመዘርዘር በአንድ ሀገር ውስጥ ስርዓት እንደሚያስከብሩ ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ዜጎች በምክክር እና በንግግር የሕግ አስፈፃሚው አካል እንዲስተካከል ብሎም እንዲቀየር በማድረግ ዜጎት በሕጋዊ ስርዓቱ ላይ አመኔታን እንዲገነቡ ያስችላል፡፡
2. የሕግ እና የሞራል ግዴታዎች መነሻነት
የሕግ ገዢነት እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት በአግባቡ እየተተገበሩ ለሕዝብ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ይህም ሲሆን የሞራል ግዴታዎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑ ሳይዘነጋ ነው፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በንግግር የሞራል ሕጎችን (ያልተፃፉ የሕሊና ሕጎች) እና የተፃፉ ሕጎችን በድጋሚ በመቃኘት እና በማስተሳሰር ቅቡልነት ያለው የፍትሕ ስርዓት እንዲገነባ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡
3. የቆሙለት ዓላማ
እንደሚታወቀው የሕግ ገዢነት እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ እኩልነት እና ነፃነት ሰፍኖ ፍትሕ እና ርትዕ ያለባትን ሀገር ለመገንባት ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ከላይ የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጋዊ ስርዓቱ በግልፅ እና በጥልቀት እንዲቃኝ ከማስቻሉም በላይ መተማመን የተፈጠረበት የሕግ-ገዢነት እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት እንዲገነባ ያስችላል፡፡