በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ስድስት ተጨዋቾች መቀየር እንደሚቻል ያውቃሉ?

You are currently viewing በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ስድስት ተጨዋቾች መቀየር እንደሚቻል ያውቃሉ?

AMN – ህዳር ዐ1/2ዐ18 ዓ/ም

በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ አንድ ቡድን ሶስት ተጨዋቾችን ቀይሮ ሲያስገባ ለበርካታ ዓመታት ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጥፍ ያደገበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡

እኤአ በ2020 ተከስቶ በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የእግር ኳስ ውድድሮች ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጠው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የወረርሽኙን ስርጭት በአጭር ጊዜ መግታት ባለመቻሉ ገደቦች ተቀምጠውና ማሻሻያዎች ተደርገው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ያለ ደጋፊ እንዲደረጉ ተወስኖ ነበር፡፡

በሽታው የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳ በመሆኑ ክለቦች በየጨዋታው አምስት አምስት ተጨዋቾችን ቀይረው ማስገባት እንዲችሉም ፍቃድ ተሰጣቸው፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ ረገብ በማለቱ ወደ ሶስት ተጨዋቾች የቅያሪ ህጉ ቢመለስም ብዙ ሳይቆይ በድጋሜ አምስት ተጨዋቾች መቀየርን ፈቀደ፡፡ ተቀያሪ ተጨዋቾች በሶስት ዙር ብቻ መግባት እንደሚችሉም በግልጽ ያሳስባል መመሪያው፡፡

ክለቦች በእረፍት ሰዓት የሚያደርጓቸው ቅያሬዎች በሶስቱ ዙሮች ውስጥ ስለማይካተቱ አራተኛ እድል ተደርጎ ተካቷል፡፡

ክለቦች ስድስት ተጨዋቾች መቀየር የሚችሉበት እድል እንዳለም የተሻሻለው መመሪያ ይጠቁማል፡፡

ከተጋጣሚ ክለቦች መካከል በጭንቅላት ጉዳት የሚወጣ ተጨዋች ካለ ሁለቱም ክለቦች ስድስት ተጨዋቾችን መቀየር እንደሚችሉ የተሻሻለው መመሪያ ይጠቅሳል፡፡

ቅዳሜ ማንችስተር ዩናይትድ ከቶትንሃም 2ለ2 ሲለያይ ቤንጃሚን ሼሽኮ በጉልበት ጉዳት በመውጣቱ ቀያይ ሰይጣናቹ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በአስር ተጨዋቾች መጫወታቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ትናንት አስቶን ቪላ በርንማውዝን 4ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ተጫዋች በጭንቅላት ጉዳት በማጣታቸው ስድስት ስድስት ተጫዋቾችን ቀይረዋል።

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review