አየር ሃይላችን የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ምልክት ነው

You are currently viewing አየር ሃይላችን የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ምልክት ነው

AMN- ሕዳር 02/2018 ዓ.ም

የኢፌዲሪ አየር ሃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ከወዲሁ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢፌዲሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ አየር ሃይላችን የኢትዮጵያ የሉአላዊነት ምልክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ ሃገር ነች፤ የምንለው በምክንያት ነው ያሉት ዋና አዛዡ፣ ይህም በዓለም በአየር ሃይል ምስረታ ግንባር ቀደም ታሪክ ካላቸው ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ባለፉት 90 ዓመታት የሃገርን ክብር እና ሉአላዊት እያስከበረ የመጣ ተቋም ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ተቋሙ የሃገርን ሉአላዊነት ከመቼውም በላይ ለማስከበር ተቋማዊ ግንባታ እና የውጊያ መሰረተ ልማት ግንባታ እያከነወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም አየር ሃይሉ ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም እንዲሆን ተደርጐ እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህንን ታላቅ ተቋም ባለፉት 90 አመታት ያለፈባቸውን ወጣውረዶች እና ያገኛቸውን ስኬቶችን ለህዝቡ ለማስተዋወቅ “ለአየር ሃይል ዕድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ የ10 ኪ.ሜ ሩጫ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ እንደሚካሄድ ዋና አዛዡ ገልፀዋል።

በቢሾፍቱ ከተማ ህዳር 21/2018 ዓ.ም ከሚከናወነው የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ሩጫ ባሻገር ኮንፈረንሶች ፣ ኤክስፓ፣ ኤግዚብሽን እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የአየር ትርዒት እንደሚካሄድ ዋና አዛዡ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገልፀዋል።

የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሚከናወነው የጐዳና ላይ ሩጫ የቢሾፍቱ ከተማ በቂ ዝግጅት ማድረጉንና ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

የምስረታ በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያነሱት ዋና አዛዡ፣ ሁሉም ዜጋ እንዲሳተፍ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ለሩጫ የተዘጋጀውን ቲሸርትም አስተዋውቀዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው የመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review