ወጣቶች የሚፈጥርላቸውን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ሊለውጡ ይገባል ሲሉ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና ገለፁ።
ይህ የተገለፀው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአንድ ጀንበር ብቻ ለ2000 የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠሩን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ነው።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና ባለፉት ስድስት ወራት በክፍለ ከተማው ስራ ፈላጊዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀው፤ ክፍለ ከተማው ስራ ፈላጊዎችን ከተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር በማስተሳሰር የስራ ባለቤት እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል ብለዋል።
ወጣቶች የሚፈጥርላቸውን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ሊለውጡ እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈፃሚው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ በ 2018 በጀት ዓመት ከ 21ሺህ በላይ ለሚሆኑ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውቢት ዮሃንስ ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ብቻ ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።
የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው እራሳቸውን ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎች እና ድርጅቶች ለስራ ዕድል ፈጠራ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው በመድረኩ ተመላክቷል።
በመሀመድኑር አሊ