‎የአየር ሃይሉን የምስረታ በዓል በማስመልከት የሚዘጋጀው ሩጫ የቢሾፍቱ ከተማን የቱሪዝም ማዕከልነት የሚያጠናክር ነው

You are currently viewing ‎የአየር ሃይሉን የምስረታ በዓል በማስመልከት የሚዘጋጀው ሩጫ የቢሾፍቱ ከተማን የቱሪዝም ማዕከልነት የሚያጠናክር ነው
  • Post category:ቱርዝም

AMN – ሕዳር 02/2018 ዓ.ም

‎የአየር ሃይሉን የምስረታ በዓል በማስመልከት የሚዘጋጀው ሩጫ የቢሾፍቱ ከተማን የቱሪዝም ማዕከልነት የሚያጠናክር መሆኑ ተገለፀ፡፡

90ኛው የኢትዮጵያ አየር ሃይል የምስረታ በዓል “ለአየር ሃይል ዕድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዳር 21/2018 ዓ.ም የሰባት ሀይቆች ባለቤት በሆነችው ቢሾፍቱ ከተማ ይካሄዳል።

መርሃ ግብሩን በተመለከተ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ንግግር ያደረጉት የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ፣ ከተማዋ ይህንን ዕድል ማግኘቷ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

ቢሾፍቱ ከተማ የጨፌ ኦሮሚያ በአዋጅ ቁጥር 250/2015 የቱሪዝም ከተማ እንድትሆን በወሰነው መሰረት፣ ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፣ አሁን የሚከናወነው የጐዳና ላይ ሩጫ ተጨማሪ ድምቀት መሆኑን ገልፀዋል::

ሩጫው የሚከናወንበት የሆረ አርሰዴ ሃይቅ ዙሪያውን ለውድድሩ ምቹ ሆኖ ከመዘጋጀቱ ባለፈ፣ በከተማዋ በሚገኙ ሃይቆች ዙሪያ ያሉ ቦታዎች ለመዝናኛ ዝግጁ ሆነዋል ያሉት ከንቲባው፣ ከተማዋ በኮሪደር ልማት ስራዎችም ሳቢና ፅዱ ሆናለች ሲሉ ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በበኩላቸው፤ በወድድሩ ስመ ጥር የሃገራችን አትሌቶችን ጨምሮ ከ25ሺ በላይ ነዋሪዎች እና የበዓሉ ታዳሚዎች እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ አትሌቶች እንደሚሳተፉ አመላክተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ውድድሮች መካሄዳቸው ለአትሌቲክሱ ትልቅ ዓቅም ይፈጥራል ያሉት ኮማንደር ስለሺ ስህን፤ አየር ሃይል ከዚህ ቀደም በሃገራችን አትሌቲክስ የነበረውን ታሪክ የሚያድስ ነው ብለዋል።

ለሩጫ ውድድሩ ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ ተሳታፊዎችና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review