ትዳርን ለማጽናት የሃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚና አላቸው

You are currently viewing ትዳርን ለማጽናት የሃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚና አላቸው

AMN- ህዳር 3/2018 ዓ.ም

ትዳርን ለማጽናት የሃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚና አላቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ትዳር የሁሉ ነገር መሰረት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በትዳር ውስጥ ቤተሰብ ይገነባል፤ በቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ሀገር ትሰራለች በማለት ገልጸዋል። በትዳር መበተን እና መፍረስ ውስጥ ሀገር እንደምትጎዳ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ልጆችም ለተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚዳረጉ አንስተዋል።

ለውጤታማ የልጆች አስተዳደግ እና የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ የተረጋጋ ትዳር የሰመረ ክዋኔ እንደሚያስፈልግም ነው ሀሳባቸውን ያጋሩት።

ይህ የቤተሰብ ውቅር የሆነውን ትዳር መሰረት ለመጠበቅ እና የተቃና ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል? ብሎ ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የባለትዳሮች ድርሻ ከፍተኛ ቢሆንም የሃይማኖት ተቋማት ሚና እጅግ የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሞላልኝ ማሩ፣ ባለትዳሮች የሚገጥማቸውን አለመግባባት ተነጋግረው መፍታት እየቻሉ ጉዳያቸውን ይዘው ፍቺ ፍለጋ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡

የትዳር መፍረስ ከሁሉ በላይ ልጆች ላይ ጥሎ የሚያልፈው ጠባሳ ከባድ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሞላልኝ ማሩ፣ በፈረሰ ትዳር ውትጥ ያደጉ ላጆች ደግሞ፣ እናታቸውን ወይ አባታቸው በሚጠይቁበት ሰዓት አትጠይቀኝ/ቂኝ እየተባሉ እና ስለጠየቁት ቤተሰብ አሉታዊ ነገር እየተነገራቸው ካደጉ ስነልቦናዊ ተጽዕኖው ከባድ ነው ብለዋል።

መግባባት፣ መቻቻል እና መከባበር ሲኖር የሃይማኖት አባቶችንም ሆነ የታላላቆችን ምክር መስማት እና ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል አብሮነት ይጸናል ብለዋል፡፡

ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ አንዋር ሀሰን በበኩላቸው፣ በባለትዳሮች መካከል የሚኖር ጭቅጭቅ ለችግሮቻቸው መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል እና በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ባለትዳሮች ብዙ ጊዜአቸውን የሚያሳልፉት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመሆኑ ለልጆቻቻው እና ለትዳራቸው ትኩረት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡

የድሮ ወላጅ ልጆቹን ለመከታተል፣ ለመገሰጽ እና ለማስተማር ጊዜ እንደነበረው በንጽጽር በመጥቀስ፣ እንደ መፍትሄም የሃይማኖት ተቋማት ትዳርን ስለማጽናት ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

ወ/ሮ መንበረ ገብረ ሚካኤል፣ የትዳር አጋሮች ደስታም ሆነ ሀዘን ማግኘት እና ማጣት ሊያጋጥማቸው ቢችልም ተረጋግተው መኖር እንጂ ትተው መሄድ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በትዳር መፍረስ እና በጋብቻ ውሎች መቀደድ በርካቶች የተለያዩ ጉዳቶችን እንደሚያስተናግዱ እና በተለይ ደግሞ ልጆች የጉዳቱ ሰለባ ናቸው ብለዋል።

ወደ እምነት ተቋማት መሄድ እና የአባቶችን ምክር መስማት ትልቅ መፍትሄ መሆኑንም ያመላክታሉ።

በፍሬህይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review