የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከዓለም አቀፍ ህጎች አንጻር ተቀባይነት ያለው ጥያቄ መሆኑን የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኪያ ፀጋዬ ገለፁ፡፡
አቶ ኪያ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ህጋዊና ዲኘሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ መሆኑን አስረድተው፣ በየትኛውም መንገድ የባህር በር ባለቤትነቷን ታስከብራለች ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር ህግ ላይ በአንቀጽ 125 እና 127 ወደብ የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ካላቸው ሀገራት ወደቦችንና መተላለፊያ ኮሪደሮችን የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷ ከአለም እቀፍ ህጎች አንፃር ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የባህር በር ማግኘቷ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗን ጠቅሰው፣ ከዓለም አቀፍ ህጎች በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ በህዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋት፣ በኢኮኖሚ እና በተፈጥሮ ሀብት ትልቅ ሀገር መሆኗ በራሱ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ማሳያ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የባህር በር ለሀገር ህልውና ጠቃሚ መሆኑን የተረዳ ትውልድ መነሳቱን ያስረዱት አቶ ኪያ፣ ትውልዱ የባህር በር ጥያቄን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስተጋባት የተጀመረበት ወቅት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

መንግስትን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ያለምንም ልዩነት በጉዳዩ ላይ አቋም ይዞ መንቀሳቀስ መጀመሩ ትውልዱ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር እንዲተጋ እድልን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
በአንድ ወቅት ጥያቄውን ማንሳት የሚያሸማቅቅ እንደነበር አስታውሰው፤ ተስፋፊ እና የሌላ ሀገር ሉአላዊነትን ለመድፈር የሚነሳ ጥያቄ ነው ተብሎ ይፈረጅ ነበር ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
በተለይ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ይህን ጉዳይ ማንሳት ነውር ነበር ያሉት አቶ ኪያ፤ ከዚያን ወቅት ወዲህ ያለው ትውልድ ስለ ወደብና የባህር በር አስፈላጊነት ብዙም ያልተረዳ ነበር ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በተሰራው የተግባቦት ሥራ የባህር በር ያለው እና የሌለው ሀገር ልዩነትን በሚገባ በመረዳት ጥያቄውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተጋባት ላይ የሚገኝ ትውልድን ማየት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጐት ኤርትራን ጨምሮ አንዳንድ የጎረቤት ሀገራት አይዋጥላቸውም ያሉት አቶ ኪያ፣ በተለይ የኢትዮጵያን እድገት ከማይመኙ ሀገራት ግብጽ ቀዳሚ መሆኗን አንስተዋል።
በኤርትራ አሁን ላይ ያለው ትውልድ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጤነኛ የሆነ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲመሰረት የሚፈልጉ በርካታ የኤርትራ ሀይሎች መኖራቸውንም አቶ ኪያ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝብ ይህንን ጤነኛ አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ በመደገፍ የወደብ ባለቤትነቱን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው